የመስቀል ደመራ በአልን ስናከብር ፍቅርን፣ አብሮነትንና መተሳሰብን በማጎልበት ሊሆን ይገባል- ብጹዕ አቡነ ዮሴፍ - ኢዜአ አማርኛ
የመስቀል ደመራ በአልን ስናከብር ፍቅርን፣ አብሮነትንና መተሳሰብን በማጎልበት ሊሆን ይገባል- ብጹዕ አቡነ ዮሴፍ
ሀዋሳ ፤መስከረም 16/2019 (ኢዜአ) :- የመስቀል ደመራ በአልን ስናከብር ፍቅርን፣ አብሮነትንና መተሳሰብን በማጎልበት ሊሆን ይገባል ሲሉ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሲዳማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶሱ አባል ብጹዕ አቡነ ዮሴፍ አስገነዘቡ።
የመስቀል ደመራ በዓል በሀዋሳና አካባቢው በተለያዩ ሀይማኖታዊ ስነ ስርአቶች ተከብሯል።
በበዓሉ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት ብጹእ አቡነ ዮሴፍ፤ የመስቀል ደመራ በአልን ስናከብር ፍቅርን፣ አብሮነትንና መተሳሰብን በማጎልበት መሆን እንዳለበት አንስተዋል።
በመሆኑም ምእመናን ለሀገር ሰላምና ልማት ይበልጥ በመቀራረብና በመተሳሰብ ለመስራት በመዘጋጀት መሆን ይኖርበታል ሲሉ ተናግረዋል።
የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጥራቱ በየነ፤ በበኩላቸው የደመራው አንድ ላይ መሰባሰብ አንድነትና አብሮነትን የሚያሳይ መሆኑን አንስተው እኛም ተደምረን ሰላምን ማጽናትና ልማትን ማስቀጠል ይገባናል ብለዋል።
በዓሉ የይቅርታና አብሮነት እንደመሆኑ የተቸገሩትን በማሰብና በመጠየቅ ማክበር እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ሀዋሳ ከተማ መንግስት በሰጠው ትኩረትና በነዋሪው ትብብር እየተሰሩ ያሉ የልማት ስራዎች የከተማዋን ገጽታ በመለወጥ፣ተመራጭና ተወዳዳሪ ከማድረግ ባለፈ የቱሪዝም ስበት ማዕከል እያደረጋት ይገኛል ብለዋል።
በዚህም የኢኮኖሚ መነቃቃት መፈጠሩን አንስተው ይህም ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል በመፍጠር ተጠቃሚ እያደረገ እንደሚገኝ ጠቅሰው ይህም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ገልጸዋል።
በሀዋሳ መስቀለ ክርስቶስ አባ ገሪማ ገዳም አስተዳዳሪ መላዓከ ኤዶም ቀሲስ ተዋበ ምትኩ፤ የመስቀል ደመራ በዓል የአንድነት፣ የመሰባሰብና የፍቅር መገለጫ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የበዓሉ ታዳሚዎችም ከደመራው መሰባሰብ፣ ፍቅርና አብሮነትን በተማርነው መሰረት ለሀገራችን ለመስራት ተዘጋጅተናል ብለዋል።