የመስቀል ደመራ በዓል የሰላምና የይቅርታ በዓል ነው- ብፁዕ አቡነ አብረሃም - ኢዜአ አማርኛ
የመስቀል ደመራ በዓል የሰላምና የይቅርታ በዓል ነው- ብፁዕ አቡነ አብረሃም
ባህርዳር፤ መስከረም 16/2019 (ኢዜአ)፦ የመስቀል ደመራ በዓል የሰላምና የይቅርታ በዓል በመሆኑ ምእመኑ በዓሉን ሲያከብር ሃይማኖታዊ ስርአቱ የሚያዘውን በመተግበር መሆን አለበት ሲሉ የባህርዳርና ሰሜን ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብፁዕ አቡነ አብረሃም ገለጹ።
የመስቀል ደመራ በዓል በባህር ዳር ከተማ የሃይማኖት አባቶች፣ ከፍተኛ የመንግስት አመራሮችና ምእመናን በተገኙበት በታላቅ ድምቀት ተከብሯል።
ብፁዕ አቡነ አብረሃም በዓሉን አስመልክተው ባስተላለፉት መልእክት እንደገለጹት ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል ፍቅር የተገለጸበት በመሆኑ እስከ ዛሬ ድረስ በድምቀት እየተከበረ ለትውልድ የሚተላለፍ ጸጋ ለመሆን መብቃቱን ገልጸዋል።
የመስቀል ደመራ በዓል የሰላምና የይቅርታ በዓል መሆኑን ተናግረዋል።
ወጣቱ ትውልድም ከመስቀል በዓል ሊማር የሚገባው ዋናው ነገር ፍቅርን፣ አንድነትንና አንዱ ለአንዱ መደጋገፍን መሆኑን ጠቁመዋል።
በዓሉ በድምቀትና በስኬት እንዲከበር አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።
የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ጎሹ እንዳላማው በበኩላቸው ምእመኑ የፍቅርና የመተሳሰብ ተምሳሌት የሆነውን የመስቀል በዓልን ሲያከብር ለዘላቂ ሰላም መስፈን በመትጋት መሆን አለበት ብለዋል።
የመስቀል ደመራ በዓል ሳይበረዝና ሳይከለስ በድምቀት በማክበር ጎብኝዎችን በመሳብ ለኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማዋል እየተሰራ ያለው ስራ ሊጠናከር ይገባል ሲሉም አመልክተዋል።
በዓሉን በበለጠ በማስተዋወቅና ለገጽታ ግንባታ በማዋል ለሀገር የልማት ከፍታና ለዘላቂ ሰላም ግንባታ ለማዋል በጋራ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ምእመኑና ወጣቱ እንደ ደመራ ችቦ በመደመር ለከተማችን ልማትና ሰላም ቀጣይነት ተባባሪነቱን አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባዋል ሲሉም መልእክት አስተላልፈዋል።
በዓሉ የሀይማኖቱ መሪዎች፣ የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር አመራሮች፣ ምእመናንና እንግዶች በተገኙበት ደመራ በመለኮስ ተጠናቋል።