ኢትዮጵያውያን ለሀገራቸው ዘላቂ ሰላምና አንድነት መረጋገጥ አበክረው ሊሰሩ ይገባል - ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያውያን ለሀገራቸው ዘላቂ ሰላምና አንድነት መረጋገጥ አበክረው ሊሰሩ ይገባል - ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 16/2019(ኢዜአ) ፦ ኢትዮጵያውያን ለሀገራቸው ዘላቂ ሰላምና አንድነት መረጋገጥ አበክረው እንዲሰሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ገለጹ።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን በአደባባይ በድምቀት የሚከበረው የመስቀል ደመራ በዓል በመስቀል አደባባይ በደማቅ ሥነ-ሥርዓት እየተከበረ ነው፡፡
በክብረ በዓሉ ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ ብጹዓን አባቶች፣ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ፣ ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች፣ ምዕመናን ፣ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮችና ጎብኚዎች ተገኝተዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ የመስቀል በዓል በመከራ መስቀል ህይወቱን አሳልፎ ህይወታችንን የማያልፍ ህይወት ያደረገውን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የምናስብበት ነው ብለዋል።
ክርስቶስ በመስቀሉ ያስተማረንን ፍቅር እና ዋጋ በህይወታችን ልንተገብረው ይገባል ያሉት ፓትሪያርኩ መስቀል የሚያስተምረን ሰላም፣ አንድነት፣ ፍቅር፣ ይቅርታንና ስምምነትን ነው ሲሉም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያውያን ለአንድነታችንና አብሮነታችን እንቅፋት የሆኑ ጉዳዮችን በትዕግስትና በአርቆ አሳቢነት በማለፍ ለተሟላ ሀገራዊ ሰላምና አንድነት መረጋጋጥ አበክረን ልንሰራ ይገባል ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
ብጹዕነታቸው ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች ለመስቀል በዓል እንኳን አደረሳችሁ በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።