ቀጥታ፡

የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ለዓለም ሰላምን የምንሰብክበት ትልቁ ምልክታችን ነው

አዲስ አበባ፤ መስከረም 16/2019 (ኢዜአ)፦ ኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ለዓለም ሰላምን የምንሰብክበት ትልቁ ምልክታችን ነው ሲሉ የሕንድ ማላንካራ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ ባስልዮስ ማርቶማ ማቴዎስ ሣልሳዊ ገለጹ።

የደመራ በዓል በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ በሃይማኖታዊ ሥነ-ሥርዓቶች እየተከበረ ነው፡፡

በሥነ ሥርዓቱ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘ ኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘ አክሱም ወጨጌ ዘ መንበረ ተክለሃይማኖት፣ የሕንድ ማላንካራ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ ባስልዮስ ማርቶማ ማቴዎስ ሣልሳዊ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የባህል እና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ፣ ብፁዓን አባቶች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ሀላፊዎች፣ ዲፕሎማቶች ታድመዋል።


 

የሕንድ ማላንካራ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ ባስልዮስ ማርቶማ ማቴዎስ ሣልሳዊ በመስቀል ደመራ በዓል ስነ ስርዓቱ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የመስቀል ደመራ በዓልን በኢትዮጵያ ለማክበር በመገኘቴ ደስተኛ ነኝ ብለዋል።

ኢትዮጵያ እና ህንድ ከበርካታ ዓመታት የዲፕሎማሲና የታሪክ ግንኙነት ባለፈ የሃይማኖትና የባህል ትስስራችን ጠንካራ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

ዛሬ በኢትዮጵያ አዲስ አበባ የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ከፍ ተደርጎ ተይዟል፤ ለዓለም ታይቷል ሲሉም ገልጸዋል።

የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ለዓለም ሰላምን የምንሰብክበት ትልቁ ምልክታችን ያሉት ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ ባስልዮስ፤ መስቀል የሰላም ምልክት በመሆኑ በዩኔስኮ በዓለም አቀፍ ደረጃ በማይዳሰስ ቅርስነት መመዝገቡ ለዓለም ትልቅ ሀብት መሆኑን እንደሚያሳይ ተናግረዋል።

ዩኔስኮ ለደመራ በዓል እውቅና መስጠቱና ዓለም እንዲያከብረው መደረጉ መስቀል የአንድነት ምልክት እንደሆነ ያሳያል ነው ብለዋል ብፁዕነታቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም