ቀጥታ፡

እንደ መስቀል ያሉ የአደባባይ በዓላት አብሮነትንና ህብረ ብሔራዊነትን የሚያጠናክሩ ማህበራዊ እሴቶች ናቸው - ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 16/2019(ኢዜአ)፦ እንደ መስቀል ያሉ የአደባባይ በዓላት አብሮነትንና ህብረ ብሔራዊነትን የሚያጠናክሩ ማህበራዊ እሴቶች መሆናቸውን የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ገለፁ።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን በአደባባይ በድምቀት የሚከበረው የመስቀል ደመራ በዓል በመስቀል አደባባይ በደማቅ ሥነ-ሥርዓት እየተከበረ ነው፡፡


 

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ በዚሁ ወቅት እንዳሉት የመስቀል በዓል የሃይማኖት ስርዓት መገለጫ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያውያን የጋራ ማንነት እና እሴቶቻችን መገለጫም ጭምር ነው።

እንደ መስቀል ያሉ የአደባባይ በዓላት አብሮነትና ህብረ ብሔራዊነትን የሚያጠናክሩ ማህበራዊ እሴቶች መሆናቸውንም አመልክተዋል።

በተጨማሪም የዜጎችን ማህበራዊ መስተጋብር በማጠናከር ረገድ ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የዘመናት ጉምቱ ታሪክ ባለቤት እና የጽናት ተምሳሌት መሆኗንም ገልጸዋል።

ቤተ ክርስቲያኗ የመስቀል በዓልን ጠብቃ በማቆየት ለትውልዱ ማድረሷና ከሀገር አልፎ ዓለም አቀፍ እውቅና እንዲያገኝ ማድረግ መቻሏን አንስተዋል።


 

ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታተ ፈተናዎችን በአይበገሬነትና በድል እያለፈች በበርካታ ዘርፎች ስኬት ማስመዝገቧን ሚኒስትሯ አንስተዋል።

ስኬቶቹ የተገኙት በብርቱ ስራ፣ በህዝቡ የጋራ ጥረት እና በትብብር በተከናወኑ ተግባራት መሆኑን አመልክተዋል።

ከትናንት ወረቶች ላይ የዛሬ ስኬቶችን በመጨመር ነገ የበለጸገች ሀገር ለመገንባት በተለይም የባህር በር ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ ኢትዮጵያውያን እንደ ደመራ ችቦ እጅ ለእጅ ተያይዘን የምንተጋበት ጊዜ አሁን ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም