ቀጥታ፡

የመስቀል በዓል ተደምረን በአብሮነትና በአንድነት የምናከብረው ነው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 16/2019(ኢዜአ)፦ የመስቀል በዓል ተደምረን በአብሮነትና በአንድነት የምናከብረው ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለፁ።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን በአደባባይ በድምቀት የሚከበረው የመስቀል ደመራ በዓል በመስቀል አደባባይ በደማቅ ሥነ-ሥርዓት እየተከበረ ነው፡፡

በክብረ በዓሉ ላይ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣ የሕንድ ማላንካራ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ ባስልዮስ ማርቶማ ማቴዎስ ሣልሳዊ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የባህል እና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ፣ ብፁዓን አባቶች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች፣ ዲፕሎማቶች ታድመዋል።


 

የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበዓሉ ላይ ባስተላለፉት መልእክት ለመስቀል በዓል እንኳን በሰላምና በጤና አደረሳችሁ ብለዋል።

በከተማችን በድምቀት ከሚከበሩ የአደባባይ በዓላት አንዱ የሆነው መስቀል ለዘመናት ሃይማኖታዊ እሴቱን ጠብቆ የቆየ ታላቅ በዓል ነው ብለዋል።

የክርስትና እምነት ተከታዮች ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል የከፈለውን ዋጋ እና ፍቅር በመያዝ ሊኖሩ ይገባል ብለዋል።

ይህም በመያዝ ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን ወሳኝ ሚና እንዳለው አመልክተዋል።

መስቀል በዩኔስኮ ተመዝግቦ የሰው ልጅ ወካይ ቅርስ በመሆን በዓለም ገጽታችንን ከፍ ያደረገ የጋራ እሴታችን ነው ብለዋል።

በደመራው ዙሪያ ነጣላ ችቦዎች ተደምረው እንደሚበሩ ሁሉ በጋራ ከቆምን ስኬታማ መሆን እንችላለን ብለዋል።

አዲስ አበባ ከተማ የዓለም የስበት እና የለውጥ ማዕከል መሆኗንና ዓለም አቀፍ ሁነቶችን እያስተናገደች እንደምትገኝ ተናግረዋል።

እንደ መስቀል ያሉ የአደባባይ በዓላት ደግሞ የሀገር ገጽታን በመገንባት፣ እንግዳ የመቀበል እሴት የሚታይበትና ቱሪስቶችን በሰፊው እየሳበ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም