ኢትዮጵያ - የዓለም የቱሪዝም ዓይን ማረፊያ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ - የዓለም የቱሪዝም ዓይን ማረፊያ
መግቢያ
በኢትዮጵያ ወርሃ መስከረም እና የዓለም የቱሪዝም ቀን ግንኙነታቸው በጣም ጥብቅ ነው። በኢትዮጵያ በወርሃ መስከረም ሁለት ትልልቅ ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ ህዝባዊ በዓላት ይከበራሉ፤ የመስቀል ደመራ በዓል እና ኢሬቻ። በመስከረም 17 ደግሞ ዓለም አቀፍ የቱሪዝም ቀን ይከበራል። በዚህም ወርሃ መስከረም ለኢትዮጵያም ሆነ ለዓለም ቱሪዝም ዘርፍ ልዩ ወር ነው።
በየዓመቱ በመስከረም 17 በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከበረው የዓለም የቱሪዝም ቀን የዘርፉን ማህበራዊ፣ ባህላዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ እሴቶች ለማስተዋወቅ እና ለማጎልበት በማለም የሚከበር ቀን ነው። ይህ ቀን ለመጀመሪያ ጊዜ የተከበረው እ.ኤ.አ. በ1980 ወይም በኢትዮጵያ 1972 መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። ቀኑ የተመረጠበት ዋና ምክንያትም እ.ኤ.አ. በ1970 የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መመሥረቻ ሕግ የፀደቀበትን ታሪካዊ ዕለት ለመዘከር በማሰብ ጭምር ነው።
የዓለም ቱሪዝም ቀን ለምን ይከበራል?
የዓለም የቱሪዝም ቀን ከሚከበርባቸው ዋና ዋና ምክንያቶች መካከል፤ የቱሪዝም ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እሴትን በማሳደግ ቱሪዝም ለሀገራት ኢኮኖሚ ዕድገት፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ እና ለውጭ ምንዛሬ ግኝት የሚያበረክተውን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ለማጎልበትና ትኩረት እንዲያገኝ፤ የባህል ልውውጥንና ዓለም አቀፍ ግንኙነትን በማጠናከር በህዝቦችና በባህሎች መካከል መልካም ግንኙነት፣ መከባበርና መረዳዳት እንዲፈጠር ለማስቻል እንዲሁም የዓለምን ብዝሃ-ባህል ለማስተዋወቅ ነው።
በተጨማሪም ዘላቂ የቱሪዝም ልማትን በማስፋፋት የተፈጥሮ፣ የታሪክና የባህል ሀብቶች ሳይበላሹና ሳይደፈርሱ ለተከታታይ ትውልድ እንዲተላለፉ የአካባቢ ጥበቃን ያገናዘበ የቱሪዝም አጠቃቀምን ለማስረጽ፤ እንዲሁም የተባበሩት መንግሥታት የዘላቂ ልማት ግቦችን በማሳካት ቱሪዝም ድህነትን በመቀነስ፣ የሥራ ዕድል በመፍጠር እና የአካባቢ ጥበቃን በማጠናከር በኩል ያለውን ሚና ለማሳወቅም ጭምር ነው።
ኢትዮጵያም በመደመር መንግስት እሳቤ በመመራት በዩኔስኮ ለተመዘገቡ የቱሪዝም ሀብቶቿ የምታደርገውን ጥበቃ እና እንክብካቤ በማጠናከር፤ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ተደብቀው የቆዩ አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ለኢኮኖሚዋ ዕድገት፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ እና ለውጭ ምንዛሬ ግኝት፤ እንዲሁም ያሏትን ብዝሃ-ባህሎች ለተቀረው ዓለም በተገቢው መንገድ ለማስተዋወቅ በማለም አልምታለች፤ እያለማችም ትገኛለች።
ኢትዮጵያ ለዘላቂ የቱሪዝም ልማት መስፋፋት፣ የተፈጥሮ፣ የታሪክና የባህል ሀብቶች ሳይበላሹና ሳይደፈርሱ ለትውልድ ለማሻገር በትኩረት እየሰራች ትገኛለች። ለዚህም የአካባቢ ጥበቃን ታሳቢ ያደረገ የቱሪዝም አጠቃቀምን ለማስተዋወቅ እንዲሁም ለተባበሩት መንግሥታት የዘላቂ ልማት ግቦች ስኬታማነት የበኩሏን እየተወጣች እንደምትገኝ የሚያመላክቱ በርካታ ውጤቶችን አስመዝግባለች።
ኢትዮጵያ ለዓለም የገለጠቻቸው የቱሪዝም ሀብቶች
ኢትዮጵያ ለቀኑ የተመቸ ተፈጥሯዊ እና ሰው ሰራሽ ማንነት እና ሀብት የሚገኝባት ሀገር ናት። ለዚህም የረጅም ታሪክ እና ድንቅ ባህል ያላት እንዲሁም የተፈጥሮ ሀብት እና የሰው ልጅ መገኛ መሆኗን መጥቀስ ይቻላል። በተጨማሪም በቱሪዝም ዘርፍ ከፍተኛ እምቅ አቅም ያላት ሀገር እንደሆነችም የመደመር መንግስት ዘርፉን የኢኮኖሚው ሞተር ለማድረግ በማሰብ ያከናወናቸው ልማቶችና የገለጣቸው ሀብቶች እማኝ ናቸው።
የመደመር መንግስት ከቱሪዝም ዘርፉ የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማሳደግ ባለፉት ዓመታት የገነባቸው የቱሪዝም መሰረተ ልማቶች የዓለም ጎብኚዎችን ቀልብ መሳብ ከጀመሩ ሰነባብተዋል። በየዓመቱ መስከረም 17 የሚከበረው የዓለም የቱሪዝም ቀን በኢትዮጵያ የቱሪዝም እድገት ላይ ቀጣይነት ያለውና የተቀናጀ እርምጃ በመውሰድ የለሙትንና እየለሙ የሚገኙትን ድንቅ የቱሪዝም ሀብቶችን ለዓለም ማህበረሰብ ለማስተዋወቅና ለሀገር ኢኮኖሚ የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ የበለጠ ለማሳደግ ትልቅ አጋጣሚ ፈጥሯል።
እነዚህን የቱሪዝም ሀገራዊ ሀብቶች በሚገባ ለማስተዋወቅ ደግሞ ዘመኑ የፈጠራቸውን የዲጂታል እና ቴክኖሎጂ ውጤቶች መጠቀም ወቅቱ የሚጠይቀው አስገዳጅ ጉዳይ ነው። ለዚህም ነው የቱሪዝም ሚኒስቴር በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ47ኛ ጊዜ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ39ኛ ጊዜ የሚከበረውን የዓለም የቱሪዝም ቀን "ዲጂታል አጀንዳ እና ሰው ሰራሽ አስተውሎት ለቱሪዝም አዲስ ቅኝት" በሚል መሪ ሀሳብ ለማክበር የተዘጋጀው።
ኢትዮጵያ በዩኔስኮ ካስመዘገበቻቸው ቅርሶች መካከል በታሪካዊና ባህላዊ ዘርፍ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ የአክሱም ሐውልቶች፣ የፋሲል ግቢ፣ የሐረር ጁገል ግንብ፣ የጫሞና የአባያ ሀይቆች አካባቢ ባህላዊ እሴቶችና ሌሎች የሀገሪቱን ድንቅ የታሪክ ጥልቀት የሚያሳዩ ሲሆን፤ በተፈጥሯዊ ድንቅ ስፍራዎች ዘርፍ ደግሞ የስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ፣ የኤርታ አሌ እሳተ ገሞራ፣ የዳሎል ዝቅተኛ ስፍራ፣ የባሌ ተራሮች እንዲሁም ብሔራዊ ፓርኮችና የዱር እንስሳት ማደሪያዎች ለአካባቢ ጥበቃና ለኢኮ-ቱሪዝም ምቹ ሁኔታን የፈጠሩ ናቸው።
ኢትዮጵያ በዓለም ከምትታወቅባቸው ቅርሶች መካከል የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች ይገኙበታል። ከእነዚህም መካከል በወርሃ መስከረም የሚከበረው የመስቀል ደመራ በዓል አከባበር፣ የጥምቀት በዓል፣ የፊቼ ጨምበላላ እንዲሁም የገዳ ሥርዓት ተጠቃሽ ናቸው።
ለቱሪዝም ዘርፉ እሴት የጨመረው - የኮሪደር ልማት
የመደመር መንግስት የቱሪዝም መስኩን አንዱ የኢኮኖሚው ምሰሶ በማድረግ መስራት ከጀመረ ሰነባብቷል። በዚህም በኢትዮጵያ ተደብቀው የቆዩ የቱሪዝም ሀብቶችን ማልማት የሚያስችል ሀገራዊ ዕቅድ በመንደፍ በተከናወኑ ተግባራት አመርቂ ውጤቶች ተመዝግበዋል። ለዚህም በመላ ኢትዮጵያ እየተከናወኑ የሚገኙት የኮሪደር እና የወንዝ ዳርቻ ልማቶች፣ የገበታ ለሸገር፣ የገበታ ለሀገር እና የገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች የቱሪዝም መስኩን ይዘት በማስፋት በኩል ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል፤ እየተጫወቱም ይገኛሉ።
ለዚህም በአዲስ አበባ የተገነቡት ፓርኮች፣ ሙዚየሞች፣ የወንዝ ዳርቻ እና የኮሪደር ልማት ስራዎች እንዲሁም አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎች የከተማዋን የቱሪዝም ገጽታንና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን እያሳደጉ ይገኛሉ።
አዲስ አበባን የአህጉሪቱንና የዓለም ኮንፍረንሶች፣ ኤግዚቢሽኖችና የከተማ ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ እንደ አንድነት፣ ወዳጅነት፣ እንጦጦ ፓርኮች፣ የሳይንስ ሙዚየም እና የዓድዋ ድል መታሰቢያ ያሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ተገንብተው ለአገልግሎት መብቃታቸው ለዚህ ጥሩ ማሳያዎች ናቸው።
ኢትዮጵያ በመደመር መንግስት እሳቤዎች በመመራት በመላ ሀገሪቱ በአቧራ ተሸፍነው የቆዩ የቱሪዝም ሀብቶቿን በማልማት ለአገልግሎት ባበቃችበት በዚህ ወቅት የሚከበረው የዓለም ቱሪዝም ቀን የኢትዮጵያን እውነተኛ ገጽታ ለዓለም ለማስተዋወቅ ጥሩ አጋጣሚ ይፈጥራል። ይህን ዓለም አቀፍ ቀን በመጠቀምም እነዚህን የቱሪስት መዳረሻዎች ዘመኑ በሚፈቅደው ቴክኖሎጂ እና ዲጂታል አማራጮች ለዓለም ማህበረሰብ ማስተዋወቅ ከምን ጊዜውም በላይ በትኩረት ሊሰራበት የሚገባ ጉዳይ ነው።
ለዚህ ደግሞ በጎርጎራ፣ በወንጪ፣ በጎንደር፣ በጅማ፣ በሐረር፣ በአርባ ምንጭ፣ በአፋር፣ በኮይሻ እና በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች የተገነቡት የቱሪዝም መዳረሻዎች ትልቅ ግብዓቶች ናቸው። እነዚህ የቱሪዝም መዳረሻዎች እና መዝናኛ ስፍራዎች ቱሪዝምን በማስፋፋት የአካባቢውን ማህበረሰብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያሳደጉ እና የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን በማነቃቃት በኩል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛሉ።
እንደ መውጫ
ቱሪዝም የውጭ ምንዛሬ ከማስገኘት ባሻገር የሥራ ዕድል የሚፈጥር፣ የባህል ልውውጥን የሚያፋጥንና የሀገርን ገጽታ የሚገነባ ታላቅ የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ነው። ኢትዮጵያ ያላትን የተፈጥሮ፣ የታሪክ እና የባህል ሀብቶች ከዘመናዊ አሰራርና ከመሰረተ ልማት ግንባታ ጋር አጣጥማ ለዓለም ካቀረበች እና በተገቢው መንገድ ካስተዋወቀች ከዘርፉ የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በማጎልበት በዘርፉ በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፎካካሪ የቱሪዝም መዳረሻ የመሆን ዕድሏ ከፍተኛ ነው። በዘርፉ እስካሁን የተከናወኑት አመርቂ ተግባራት እና የተመዘገቡ ውጤቶች ለመጪው ዘመን እርሾ በመሆን የሚያገለግሉ ተስፋዎች ናቸው።