በዓላት የቱሪዝም ሀብቶች የአብሮነትና የጋራ ማንነት መገለጫዎች - ኢዜአ አማርኛ
በዓላት የቱሪዝም ሀብቶች የአብሮነትና የጋራ ማንነት መገለጫዎች
የክረምቱ ወራትን ማለፍ ተከትሎ የሚመጣው የብርሀን ወቅት ብዙ እቅዶች፣ ተስፋዎች፣ ህልሞች ፈክተው የሚታዩበት እንደለመለመችው ምድር ቀልብን የሚስቡበት ጊዜ ነው።
ይህ ወቅት ደግሞ በገጠርም በከተማም ህዝቦች የሚሰባሰቡባቸው በአብሮነት የሚደምቁባቸውና በርካታ የውጭ እና የሃገር ውስጥ ቱሪስቶችን ቀልብ የሚስቡ የአደባባይ በዓላት የሚከበሩበትም ነው።
ኢትዮጵያ ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው ዘርፉ እድገት የሚሆኑ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት የተመዘገቡ በርካታ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች ያሏት ናት።
“የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ሀገራት በዘመናቸው ሁሉ የሰሩትንና ተፈጥሮ ያደለቻቸውን መልካም ገጽታ በኩራት ለዓለም የሚያስተዋውቁበት ፣ ‘ሀገሬ ይሄነን ትመስላለች’ የሚሉበት መድረክ ነው። ሀገርን በሚያኮራና ለሌሎች ለመጋበዝ በማያሳፍር መልኩ መገንባት ለቱሪዝም ኢንዱስትሪ መሰረቱ ነው” …የመደመር መንግሥት መጽሐፍ ገጽ 256
ቱሪዝምን ማሳደግ ሃገራችን ከዘርፉ ልታገኘው የሚገባትን ሰፊ ጥቅም ማረጋገጥ የመደመር መንግሥት ትኩረት ካደረገባቸው አምስቱ የኢኮኖሚ ምሰሶዎች አንዱ ነው።
በዚህም መሰረት ተፈጥሯዊ ሀብቶችን በማልማት ሰው ሰራሽ ቅርሶችንም ለተከናነባቸው አቧራ በማራገፍ ጭምር እንደገና እንዲደምቁ ጎልተው እንዲታዩ ከማድረግ ጀምሮ የህዝብ በዓላትን ትውፊታቸውን ሳይለቁ ለዓለም ማህበረሰብ የማስተዋወቁ ስራ በተጠናከረ መልኩ ቀጥሏል።
ተፈጥሯዊ ሃብቶችን በገበታ ፕሮግራሞች የማልማቱ ስራ እንዳለ ሆኖ ታሪካዊ ቅርሶች እንዲታደሱ ከተሞች ፍጹም አዲስ ገጽታ እንዲላበሱና ለነዋሪዎቻቸውም ሆነ ለእንግዶች ምቹ እንዲሆኑ የተሔደበት መንገድ በውጤት የታጀበ የሚያኮራም ነው።
በዚህ ወቅት በተለያዩ የሃገራችን ክፍሎች የሚከበሩ በዓላት የበለጠ ደምቀው እንዲታዩ በማድረግ በኩልም ትልቅ አበርክቶ አላቸው።
ኢትዮጵያ በቅርስነት ካስመዘገበቻቸው የማይዳሰሱ ቅርሶች መካከልም በዚህ ወቅት የሚከበሩት መስቀል በዓል እና የኦሮሞ የገዳ ስርዓት አካል የሆነው ኢሬቻም ይገኝበታል።
የወላይታው የዘመን መለወጫ በዓል ጊፋታ የሲዳማው ፊቼ ጫምባላላ የዚህ ወቅት የሚከበሩ የዓደባባይ በዓላት ሲሆኑ ጥምቀትን ጨምሮ በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡ የማይዳሰሱ ቅርሶችም ናቸው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአንድ ወቅት ቱሪዝም ዋና የኢኮኖሚ ምሰሶ መሆኑን ሲያብራሩ የብዝሃ ዘርፍ ሪፎርሙ ለቱሪዝም መስክ የኢኮኖሚ አበርክቶ ማደግ ትልቅ ሚና ተጫውቷል ማለታቸው ይታወሳል።
ለዚህም በማሳያነት ከጠቀሱት ጉዳይ መካከልም የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ እንዳለ ሆኖ በዘንድሮው ዓመት ከ1 ነጥብ 4 ሚሊየን በላይ የውጭ ሀገር ጎብኚዎች ኢትዮጵያን መጎብኘታቸውን አንስተዋል።
ይህም ቁጥር ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከ100 ሺህ በላይ፣ ከካቻምናው አንጻር ደግሞ የ300 ሺህ የጎብኚዎች ጭማሪ ማሳየቱን አብራርተዋል።
በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት ውስጥ ቁልፍ ሚናውን እየተጫወተ ያለው ቱሪዝም የበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የመንግሥት ትኩረት መሆኑም ይታወቃል።
በቅርስነት የተመዘገቡትንም ሆነ ሌሎችን በዓላት ለመታደም ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባውን ቱሪስት ለማሳደግና ገቢውንም ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ዘርፉን የሚያግዙ ስራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል።
እንደ ሀረር የጁገል ግንብ ፣ የአፄ ፋሲል ቤተመንግስት የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ፣ የጢያ ትክል ድንጋዮች፣ አክሱም ሐውልቶች የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ፣ የላሊበላ ውቅር አብያተ ቤተክርስቲያናት ፣የታችኛው አዋሽ ሸለቆ ያሉትን የሚዳሰሱ ተፈጥሯዊና ታሪካዊ ቅርሶች ላይ የተደረገውን ትኩረት ጨምሮ ሌሎችንም በማልማት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ማሳደግ የሃገራችንን የማንሰራራት ጉዞ ማፋጠን ወቅቱ የሚጠይቀው ጉዳይ ነው