ቀጥታ፡

አዲስ የሚመሰረተው መንግስት የሴቶችንና ወጣቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ይበልጥ ማረጋገጥ ይጠበቅበታል

አዲስ አበባ፤ መስከረም 16/2019 (ኢዜአ)፦ አዲስ የሚመሰረተው መንግስት የሴቶችና ወጣቶችን ተሳትፎና ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ይበልጥ ማረጋገጥ የሚያስችሉ ሥራዎች ላይ ማተኮር እንደሚጠበቅበት ኢዜአ ያነጋገራቸው የሴቶችና ወጣቶች ማህበራት ገለጹ፡፡

የአዲሱ መንግሥት ምሥረታ እና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መክፈቻ ሥነ ሥርዓት መስከረም 25 ቀን 2019 ዓ.ም እንደሚካሄድ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስታውቋል።

በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ከ50 ሚሊዮን በላይ መራጮች ድምጻቸውን በመስጠት ለሀገር ይጠቅማል ያሉትን የፖለቲካ ፓርቲ በመምረጥ ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ያላቸውን ጽኑ መሻት በተግባር አሳይተዋል።

ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ በተሳካ ሁኔታ እንዲካሄድ ያደረገው የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በገለጸው ውጤት መሰረት ህዝቡ ይበጀኛል ይጠቅመኛል በማለት አብላጫ ድምጽ የሰጠው ብልፅግና ፓርቲ መንግስት መመስረት የሚያስችለውን ይሁንታ ማግኘቱን ማሳወቁ ይታወሳል፡፡

የተለያዩ የፖለቲካ ፓርዎችም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትንና የክልሎች ምክር ቤቶችን መቀመጫ እንዲያገኙ ድምጽ ሰጥቷቸዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ህዝብ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት መስፈን፣ ለህግ የበላይነት መረጋገጥ ያለውን ፍላጎት በምርጫ ካርዱ በመወሰን የአዲሱን መንግሥት መመስረት በጉጉት እየጠበቀ ነው።  

የአዲስ አበባ ሴቶችና ወጣቶች ማኅበራት በአዲሱ መንግሥት ምስረታና በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የነበራቸውን ንቁ ተሳትፎ አስመልክተው ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡ 

የአዲስ አበባ ወጣቶች ማኅበር ፕሬዝዳንት በረከት ቢርቢርሳ፤ አዲስ የሚመሰረተው መንግስት የተጀመሩ የልማት ስራዎችን አጠናክሮ ይቀጥላል የሚል እምነት አለኝ ብለዋል።

በተለይም የወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት ለሚያረጋግጡ ሥራዎች ላይ በማተኮር መስራት እንዳለበትም ጠቁመዋል።

ወጣቶች በሀገር ግንባታ ላይ ጉልህ ሚና እንዳላቸው ጠቁመው፤ ወጣቶችም ለሀገር እድገት የሚጠበቅባቸውን ሚና ለመወጣት ዝግጁ መሆን ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡


 

የአዲስ አበባ ከተማ ሴቶች ማህበር ፕሬዝዳንት ወይዘሮ እናትአለም እንዳለ በበኩላቸው፤ አዲስ የሚመሰረተው መንግሥት ቀደም ብሎ ለሴቶችና ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ሲደረግ የቆየውን ጥረት ልዩ ትኩረት በመስጠት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ያላቸውን እምነት ተናግረዋል፡፡ 

መንግስት የሴቶችን ተጠቃሚነት ይበልጥ ማረጋገጥ የሚያስችሉ ትላልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች እውን በማድረግ በኩል ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባውም ነው የተናገሩት፡፡

አዲሱ መንግስት የሴቶችን ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት የበለጠ ለማረጋገጥ በሚያከናውናቸው ተግባራት ላይ ሴቶች ንቁ ተሳትፎ ማድረግ እንዳለባቸውም ነው የጠቆሙት፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም