የኢትዮጵያ የብሪክስ አባልነት አዳዲስ የኢኮኖሚ ዕድሎችን እየከፈተ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የብሪክስ አባልነት አዳዲስ የኢኮኖሚ ዕድሎችን እየከፈተ ነው
አዲስ አበባ፤ መስከረም 16/2019 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የብሪክስ ጥምረትን መቀላቀሏ በተለያዩ ዘርፎች አዳዲስ የኢኮኖሚ ዕድሎችን እየከፈተ እንደሚገኝ በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ሕይወት እሸቱ ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ልዑካቸው ''ጽናትን፣ ፈጠራን፣ ትብብርን እና ዘላቂነትን መገንባት'' በሚል መሪ ቃል በሕንድ ኒው ዴልሂ በተካሄደው 18ኛው የብሪክስ ጉባኤ ላይ መሳተፋቸው ይታወቃል፡፡
በብሪክስ አባል ሀገራት ዘንድ ሀብት፣ ቴክኖሎጂ እና ሰፊ ገበያ አለን፤ አሁን ያለው መልካም ዕድል እነዚህን አቅሞች በማስተሳሰር የላቀ እሴት መፍጠር እና ይህ እሴት ደግሞ ሀብቱ በሚገኝበት ቦታ መመረት እንዲችል ማድረግ ነው በማለትም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ኢትዮጵያ በማዕድን ልማት፣ በታዳሽ ኃይል እና እያደገ በሚገኘው የኢንዱስትሪ መሠረቷ ላይ እነዚህን አጋርነቶች ለመገንባት ዝግጁ ናትም ብለዋል።
በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ሕይወት እሸቱ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ኢትዮጵያ በብሪክስ እያደረገች ያለችው ተሳትፎ እየጎለበተ መምጣቱን ጠቁመው ይህም የኢኮኖሚ ዕድሎችን እያሰፋ ይገኛል ብለዋል።
ኢትዮጵያ አበይት ከሚባሉ የበለጸጉና ኢኮኖሚያቸው እያደገ ከሚገኙ ሀገራት ጋር እንዲሁም በዓለም አቀፍ የኢኮኖሚና ጂኦፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ በከፍተኛ ደረጃ ውይይቶች ላይ መሳተፏ የአባልነቷን ስልታዊነት ያጎላዋል ነው ያሉት።
ብሪክስ የኢኮኖሚ ስብስብ ብቻ እንዳልሆነ የገለጹት ተመራማሪዋ ይልቁንም ለኢትዮጵያ ተጨማሪ የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መድረክ ሆኖ ያገለግላል ብለዋል።
መድረኩ ኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅሞቿን እንድታስከብር ከማስቻሉ ባለፈ የዓለም አቀፍ ፋይናንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ንግድ፣ ዘላቂ ልማት እና ጸጥታን ጨምሮ በወሳኝ ዘርፎች የአፍሪካን አጀንዳዎች እንድታንጸባርቅ ዕድል መፍጠሩንም አክለዋል።
የኢትዮጵያ የብሪክስ አባልነት በጥምረቱ በተመሰረተው አዲስ ልማት ባንክ አባል መሆን እንደሚያስችል ጠቁመውም ይህም ለሰፊ የመሠረተ ልማት እና ለዘላቂ ልማት ፕሮጀክቶች የሚሆን የፋይናንስ ምንጭ ሆኖ እንደሚያገለግል ገልጸዋል።
የዚህ ባንክ የፋይናንስ ግቦች ኢትዮጵያ ከያዘቻቸው ሀገራዊ ፍላጎቶች ጋር የሚጣጣሙ መሆናቸው ኢትዮጵያ የልማት ፋይናንስ ምንጮቿን እንድታሰፋም ዕድል ይፈጥራል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ የብሪክስ ጥምረት አባልነት ለሀገሪቱ ተጨማሪ የዲፕሎማሲ ግንኙነት መድረክ ሆኖ እንደሚያገለግል ነው ተመራማሪዋ የገለጹት።
ኢትዮጵያ ስብስቡን ከተቀላቀለች ጀምሮ ከመሪዎች ጉባኤ እና ሚኒስትሮች ስብሰባዎች ጀምሮ እስከ ባለሙያዎች እና የሥራ ቡድኖች ውይይት ድረስ በንቃት እየተሳተፈች እንደምትገኝም ጨምረው አስታውቀዋል።
ይህ የብሪክስ ስብስብ ኢትዮጵያ እያደጉ ካሉ ገበያዎች ጋር በቀጥታ እንድትገናኝና የንግድ እና የኢንቨስትመንት አድማሷን እንድታሰፋ አቅም እንደሚፈጥርም አብራርተዋል።
እነዚህን ዕድሎች አሟጦ ለመጠቀም እንደ ግብርና፣ አግሮ-ፕሮሰሲንግ፣ ጨርቃጨርቅ፣ ኢነርጂ፣ ቱሪዝም እና ማዕድን ያሉ ተወዳዳሪ የሆኑ ሀገር በቀል ዘርፎችን በሚገባ ማስተዋወቅ ይገባል ብለዋል።
በተጨማሪም የብሪክስ ስብስብ ኢኮኖሚያዊ ትብብርን ለማጠናከርና የደቡብ ደቡብ ትብብር ጥቅሞችን ለማስከበር ትልቅ መድረክ ሆኖ እንደሚያገለግልም ተመራማሪዋ ጨምረው ገልጸዋል።
ከብሪክስ ስብስብ የሚገኙ ጥቅሞችን በውጤታማነት ለመጠቀም የተቀናጀ የተቋማት ተሳትፎ ማጠናከርና የኢትዮጵያን የንግድና ኢንቨስትመንት አቅም እና አማራጮች በሚገባ ማስተዋወቅ ይገባል ብለዋል።