ቀጥታ፡

በድሬዳዋ አስተዳደር የተካሔዱ ሰው ተኮር የልማት ስራዎች የማሕበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ አስችለዋል

መስከረም 16/2018(ኢዜአ)፡-በድሬዳዋ አስተዳደር እየተካሔዱ ያሉ ሰው ተኮር የልማት ፕሮጀክቶች የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ያስቻሉ ናቸው ሲሉ ከንቲባ ከድር ጁሃር ተናገሩ።

ሰው  ተኮር የልማት ፕሮጀክቶችን አጠናክሮ ለማስቀጠልም  12 ቢሊዮን ብር በጀት መመደቡም ተገልጿል።

ካለፉት አምስት አመታት ጀምሮ በድሬዳዋ አስተዳደር በገጠርና በከተማ ከ22 ቢሊየን ብር በላይ በጀት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው የልማት ፕሮጀክቶች ተግባራዊ በመደረግ ላይ ናቸው። 

በተለይ በመደመር መንግስት በከተማ እና በገጠር ተግባራዊ የተደረጉ ፕሮጀክቶች የነዋሪውን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በማሳደጋቸው በላቀ ደረጃ ተጠናክረው  እንደሚቀጥሉ ነው የተናገሩት።


 

በተጠናቀቀው ሳምንትም ለትራፊክ ክፍት የሆነውን  የ 4 ነጥብ 2 ኪሎሜትር የኮንክሪት አስፋልት መንገድ  የዚሁ አካል መሆኑም አንስተዋል።

ከንቲባ ከድር ጁሃር  በመንገዱ ምረቃ ወቅት እንደተናገሩት  በድሬዳዋ አስተዳደር ባለፉት አምስት አመታት የተተገበሩት ፕሮጀክቶች ድሬዳዋን  ውብና ተመራጭ የስራ እና የመኖሪያ ማዕከል አድርጓታል።


 

የድሬደዋ አስተዳደር የፕላንና ኢኮኖሚ ልማት ኮሚሽነር ኃይለማሪያም ዳዲ በበኩላቸው ፤ በዘንድሮ በጀት አመት የነዋሪዎችን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመፍታት 12 ቢሊዮን ብር ተመድቧል።

በዚህም 146 አዳዲስና ነባር  ፕሮጀክቶች በመተግበር ላይ ናቸው ነው ያሉት። 

ባለፉት  አምስት  አመታት 31 ግዙፍ የመንገድ፣ የንፁህ መጠጥ እና የመስኖ ፕሮጀክቶች ፣ የገበያ ማዕከላት እና የጋራ መኖሪያ ቤቶች መገንባታቸውን ነው የተናገሩት።

በዚህም የነዋሪዎችን የልማት ጥያቄዎች  ደረጃ በደረጃ ለመፍታት  መቻሉን ነው ያስታወቁት።

አስተዳደሩ  በተያዘው  በጀት ዓመት የንፁህ መጠጥ ውሃ፣ የመስኖ ፣ የአስፋልት መንገዶች፣ የኮሪደር ልማት ፣ የስራ ዕድል ፈጠራ እና  ሌሎች ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው  ጊዜ በጥራትና በፍጥነት ለማጠናቀቅ  ወደ ስራ መግባቱን ተናግረዋል።

በተጨማሪም  የመሶብ አንድ ማዕከል ዲጂታል አገልግሎት በማስፋት  የመንግስት አገልግሎት የማዘመን  ስራ ትኩረት የተሰጠባቸው ስራዎች ናቸው ብለዋል።

የኮሪደር ልማትን በማስቀጠልና  የከተማ ነዋሪዎችን የመጠጥ ውሃ ችግር በማቃለል  የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በላቀ ደረጃ ለመፍታት  ጥረቱ መቀጠሉን ተናግረዋል።

በመከናወን ላይ የሚገኙ  ፕሮጀክቶች የስራ ዕድል ፈጠራ የሚያሳድጉ ከመሆናቸው በተጨማሪ ድሬዳዋን  የኢንዱስትሪና የአገልግሎት ማዕከልነት ይበልጥ  ያሳድጋሉ ብለዋል። 


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም