ቀጥታ፡

ያሰበችውን የምታሳካ ታላቅ ሀገር : ኢትዮጵያ

ኢትዮጵያ በታሪኳ፣ በመልክዓ-ምድር አቀማመጧ እና ከ126 ሚሊዮን በላይ በሚልቀው ግዙፍ የሕዝብ ቁጥሯ የአፍሪካ ሁለተኛዋ ባለብዙ ሕዝብ ሀገር ብቻ ሳትሆን፣ አቅዶ የመስራት እና ያቀደችውን በቁጥራዊ ስኬት የመተግበር ጽናት ያላት ታላቅ ሀገር ናት።

በዛሬይቱ ኢትዮጵያ የምናየው እውነታ ደግሞ ከኖረችበት የድህነትና የእርዳታ ታሪክ በአስተማማኝ ሁኔታ በመውጣት፣ እምቅ አቅሟን ያማከለ ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ የሚደረግ ታሪካዊ የሽግግር ጉዞ ነው።

ሀገሪቱ በየዓመቱ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገበች ሲሆን፣ ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባትም ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነውን የውጭ ንግዷን በአንድ የትራንዚት መስመር ላይ ከማጥበብ ወጥታ አስተማማኝና ስልታዊ የባህር በር ባለቤትነትን ለማረጋገጥ የምታደርገው የዲፕሎማሲ ጉዞ የዚሁ ግዙፍ ስትራቴጂ አካል ነው።

ይህንን ታላቅነት በተግባር ከማረጋገጥ ማሳያዎች መካከል የኢትዮጵያ የትልቅ ራዕዮች ውጤት የሆኑት ግዙፍ ሜጋ ፕሮጀክቶች ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ናቸው።

በሀገር ውስጥ አቅምና በሕዝብ ተሳትፎ የተገነባው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ 74 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ የመያዝ አቅም ያለውና 5 ሺህ 150 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጭ ግዙፍ የኢነርጂ ፕሮጀክት ነው። ግድቡ የሀገሪቱን የኤሌክትሪክ ተዳራሽነት በእጥፍ ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ዋናው ምሰሶ ነው።

በተመሳሳይ መልኩ በዓመት እስከ 100 ሚሊዮን መንገደኞችን ለማስተናገድ የተነደፈው የቢሾፍቱ ግዙፍ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ፣ የአቪዬሽን ዘርፉን በአፍሪካ ቀዳሚና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሚያደርግ የታላቅነት ማሳያ ነው።

የሀገሪቱን ገጽታ ከመቀየርና የዜጎችን የኑሮ ደረጃ ከማሻሻል አንጻር በአዲስ አበባ እና በሌሎች ዋና ዋና ከተሞች የመንገድ፣ የእግረኛና የብስክሌት ጎዳናዎች እንዲሁም የስፖርት ማዘወትሪያ እና አረንጓዴ ስፍራዎችን ያካተተው የኮሪደር ልማት ሌላው የታላቅነት ማሳያ ነው።

ይህ የኮሪደር ልማት ከተሞችን ለኑሮና ለንግድ ተስማሚ ከማድረጉም በላይ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆኑ የገበታ ለሀገር እና የገበታ ለትውልድ የቱሪዝም ፕሮጀክቶች ጋር ተደምሮ የሀገሪቱን ያልተነኩ የተፈጥሮና የታሪክ ፀጋዎች በመጠቀም የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን እያረጋገጠ ይገኛል።

ከተረጂነትና ከእርዳታ ጥገኝነት መላቀቅ የሚቻለው በምግብ ራስን በመቻል መሆኑን የተረዳችው ኢትዮጵያ፣ በስንዴ ልማት ያመጣችው አሃዛዊ እመርታ አስደማሚ ነው። ኢትዮጵያ በዓመት 33 ሚሊዮን ቶን ስንዴ በማምረት በአፍሪካ ቀዳሚዋ ሀገር ሆናለች።

አሁን ላይ ሀገሪቱ ከውጭ ስንዴ ከማስገባት ወጥታ ለውጭ ገበያ ማቅረብ የጀመረች ሲሆን፤ ይህ የስንዴ ልማት ስኬት ከተረጂነት መላቀቅ እንደሚቻል በተግባር ያረጋገጠ ታላቅ ብሔራዊ ድል ነው።

ከተፈጥሮ ሚዛን መጠበቅ እና ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ የተጀመረው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ የሀገሪቱን የደን ሽፋን ከነበረበት ከ4 በመቶ በታች ተነስቶ አሁን ላይ 23 ነጥብ 6 በመቶ እንዲደርስ አድርጓል።

ይህ ስራ የዛሬን ፍላጎት ከነገው ትውልድ ህልውና ጋር የሚያስተሳስር ሲሆን፣ ለአካባቢ ጥበቃ እና ለስነ-ምህዳር መታደስ የተከናወነ ዓለም አቀፍ አርአያነት ያለው ስራ ነው።

እነዚህን ታላላቅ ስኬቶች ዘላቂ ለማድረግ ሀገሪቱ አጠቃላይ የማክሮ-ኢኮኖሚ ማሻሻያ በመተግበር ላይ ትገኛለች።

የውጭ ምንዛሬ ተመን በገበያ እንዲወሰን ማድረግ፣ የፋይናንስ ዘርፉን ለውጭ ኢንቨስተሮች ክፍት ማድረግ እና የንግድ አሰራር ማነቆዎችን ማስወገድ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን (FDI) በመሳብ የግሉን ዘርፍ አቅም የሚያነቃቁ ናቸው።

ኢትዮጵያ ባላት ግዙፍ የሰው ኃይል፣ የተፈጥሮ ፀጋ፣ የቴክኖሎጂና የዲጂታል አሰራር እመርታዎች እንዲሁም ባሳየችው በተግባር የተደገፈ ቁርጠኝነት ያሰበችውን የምታሳካ ታላቅ ሀገር መሆኗ የማይቀር እውነታ ነው

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም