የመስቀል ደመራ በዓል የሕዝቦችን አንድነትና አብሮነትን ይበልጥ በሚያጠናክር መልኩ ይከበራል - ኢዜአ አማርኛ
የመስቀል ደመራ በዓል የሕዝቦችን አንድነትና አብሮነትን ይበልጥ በሚያጠናክር መልኩ ይከበራል
አዲስ አበባ ፤ መስከረም 16/2019 (ኢዜአ)፦የመስቀል ደመራ በዓል የሕዝቦችን አንድነትና አብሮነትን ይበልጥ በሚያጠናክር መልኩ እንደሚከበር በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የመስቀል ደመራ በዓል አከባበር የፀጥታ ኮሚቴ ሰብሳቢ አፈ መምህር አባ ገብረሥላሴ ጌትነት ገለጹ፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የመስቀል በዓል አከባበር የፀጥታ ኮሚቴ ሰብሳቢ አፈ መምህር አባ ገብረሥላሴ ጌትነት ለኢዜአ እንዳሉት፤ የመስቀል ደመራ በዓል በታላቅ ድምቀት ለማክበር በ12 ንኡሳን ኮሚቴዎች የተደራጀው አብይ ኮሚቴ ቅድመ ዝግጅቱን አጠናቋል።
በዓሉ ለሀገር መልካም ገጽታ ግንባታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለውና የአብሮነት፣ የፍቅርና የእንግዳ ተቀባይነት እሴቶች ጎልተው የሚታዩበት መሆኑን ተናግረዋል።
በደመራ በዓል ችቦዎች አንድ ላይ ተደምረው ታላቅ ብርሃን እንደሚያስገኙ ሁሉ፣ የኢትዮጵያውያንም ህብረ-ብሔራዊ አንድነታቸውንና ብዝሃነት የአንድነታቸውና የመደጋገፋቸው መሠረት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ችቦዎች በአንድነት ተሰባስበው በሚፈነጥቁት ብርሃን መስቀሉን እንደሚገልጹ ሁሉ፣ የሕዝቡም አንድነትና ትብብር የኢትዮጵያን ታላቅነት፣ ማንነትና ሁለንተናዊ እድገት ለዓለም የሚያሳይ ዋና መሳሪያ እንደሆነ ተናግረዋል።
የመስቀል ደመራ በዓል በዩኔስኮ በማይዳሰስ የዓለም ቅርስነት የተመዘገበ ሲሆን ይህም ኢትዮጵያንና ጥንታዊ እሴቶቿን ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በበጎ መንገድ እንዲያውቃት በማድረግ የሀገርን መልካም ገፅታ እንደሚገነባ ጠቁመዋል።
ከዚህ ቀደም ቅርሱን የመጠበቅ ሀላፊነት የኢትዮጵያውያን ብቻ የነበረ ሲሆን፣ አሁን ግን በዓለም አቀፍ ደረጃ ትኩረት አግኝቶ የዓለም ሀብት በመሆኑ ጥበቃውም ዓለም አቀፋዊ ይዘት እንዲኖረው አስችሏል ነው ያሉት።
በበዓሉ ለመታደም በርካታ የውጭ ሀገር ቱሪስቶች ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጡ ገልፀው እነዚህ ጎብኚዎች የኢትዮጵያን ባህል፣ ወግ፣ ታሪክና የአኗኗር ዘይቤ ተረድተው በመመለስ በሄዱበት ሁሉ የኢትዮጵያ አምባሳደር ይሆናሉ ብለዋል፡፡
የመስቀል ደመራ በዓልን ለማክበር በ12 ንኡሳን ኮሚቴዎች የተደራጀው አቢይ ኮሚቴ አስፈላጊውን በጀት በመመደብ ዕቅዶቹን አስጸድቀው ወደ ሥራ መግባታቸውን አስታውሰዋል፡፡
በአሁኑ ወቅትም ሁሉም ንኡሳን ኮሚቴዎች የተጣለባቸውን ቅድመ ዝግጅት ሙሉ በሙሉ ማጠናቀቃቸው ጠቁመዋል፡፡