የመስቀልና የደመራ በዓል ሀይማኖታዊ እሴቱን ጠብቆ በድምቀት እንዲከበር ሁሉም አካላት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል − የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
የመስቀልና የደመራ በዓል ሀይማኖታዊ እሴቱን ጠብቆ በድምቀት እንዲከበር ሁሉም አካላት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል − የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ ፤ መስከረም 16/2019 (ኢዜአ) ፦ የመስቀልና የደመራ በዓል የሀገር ሀብት እና ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ ያስተዋወቀ ቅርስ በመሆኑ ኃይማኖታዊ እሴቱን ጠብቆ በድምቀት እንዲከበር ሁሉም አካላት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ፡፡
ከንቲባ አዳነች በዘንድሮው የመስቀል ደመራ በዓል ዝግጅት ዙሪያ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አባቶች እንዲሁም ከቤተክርስቲያኒቱ እና ከከተማ አስተዳደሩ የበዓል ዝግጅት ጥምር ኮሚቴ አባላት ጋር ተወያይተዋል፡፡
በመላው ኢትዮጵያ በድምቀት የሚከበረው እና በዩኔስኮ የዓለም የማይዳሰስ ቅርስ ሆኖ የተመዘገበው የመስቀል ደመራ በዓል በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ በሺዎች የሚቆጠሩ ምዕመናን በርካታ የውጭ ሀገር ጎብኚዎች በተገኙበት በድምቀት ይከበራል፡፡
ይህንን የሀገር ሀብት የሆነ ታላቅ በዓል ኃይማኖታዊ እሴቱን ጠብቆ በድምቀት እንዲከበር የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ጋር የበዓል ቅድመ አዘጋጅ ጥምር ኮሚቴን በማቋቋም በየዓመቱ የተለያዩ ዝግጅቶችን ያደርጋል።
የዘንድሮውን በዓል ዝግጅት በማስመልከትም ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አባቶች እንዲሁም ከቤተክርስቲያኒቱ እና ከከተማ አስተዳደሩ የበዓል ዝግጅት ጥምር ኮሚቴ ጋር የማጠቃለያ ውይይት አካሂደዋል፡፡
ከንቲባዋ በውይይቱ ላይ የመስቀል እና የደመራ በዓል የሀገር ሀብት እና ኢትዮጵያን በአለም መድረክ ያስተዋወቀ ቅርስ በመሆኑ ኃይማኖታዊ እሴቱን ጠብቆ በድምቀት እንዲከበር ሁሉም አካላት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።
የከተማ አስተዳደሩ የመስቀል አደባባይን ጨምሮ በከተማዋ ደመራ በሚደመርባቸው ከ2ሺ 657 በላይ የሆኑ ቦታዎችን በማጽዳት እና ለበዓሉ የሚሆኑ ግብዓቶችን በማሟላት አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረጉን የበዓሉ አዘጋጅ ኮሚቴ የገለጸ ሲሆን አስተዳደሩ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ጋር ተቀራርቦ በልማትም ይሁን በበዓላት አከባበር ጉዳዮች በትብብር እየሰራ በመሆኑ አባቶች ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ በሚያከናውናቸው የልማት ስራዎች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ተባባሪ በመሆን አርዓያነት ያለው ተግባር እየፈጸመች መሆኑን የተናገሩት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከቤተ ክርስቲያኗ ጋር በትብብር የመስራቱ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡