ቀጥታ፡

የኢትዮ-ጅቡቲ የነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧ ፕሮጀክት የሎጂስቲክስ ወጪን በእጅጉ የሚቀንስ ነው

አዲስ አበባ ፤ መስከረም 15/2019 (ኢዜአ)፦ በጅቡቲ ዳመርጆግና በኢትዮጵያ ደወሌ መካከል የሚዘረጋው የ120 ኪሎ ሜትር የነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧ ፕሮጀክት የነዳጅ አቅርቦትን በማቀላጠፍ የሎጂስቲክስ ችግሮችን እንደሚያቃልል የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ አስታወቀ።

ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ (EIH) እና በዳንጎቴ ግሩፕ መካከል በተደረገ አጋርነት የሚተገበር ሲሆን፤ ከ1 ሚሊዮን ኩቢክ ሜትር በላይ የተጣራ የነዳጅ ምርቶችን የመያዝ እና የማስተላለፍ አቅም ይኖረዋል።

ፕሮጀክቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ የጅቡቲው ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ዑመር ጌሌ እና የዳንጎቴ ግሩፕ ፕሬዚዳንት አሊኮ ዳንጎቴ በተገኙበት ይፋ ተደርጓል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ብሩክ ታዬ (ዶ/ር) ለ‘ፐልስ ኦፍ አፍሪካ’ እንደገለጹት፤ አሁን ባለው አሰራር ነዳጅ በጅቡቲ ወደብ ከመርከብ ወርዶ ወደ ማከማቻ ከገባ በኋላ በቦቴዎች አማካኝነት 750 ኪሎ ሜትር ያህል ተጓጉዞ ወደ ኢትዮጵያ ይገባል።

በኢትዮ-ጅቡቲ ኮሪደር በቀን ከሚጓጓዙ 1000 የጭነት ተሽከርካሪዎች መካከል 35 በመቶ የሚሆኑት ነዳጅ ጫኝ ቦቴዎች መሆናቸውንና ይህ አሰራርም ውጤታማ አለመሆኑን ገልጸው አዲሱ የቧንቧ መስመር የሎጂስቲክስ ወጪን በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚቀንስ አስረድተዋል።

በተጨማሪም በጅቡቲ ወደብ የቦቴዎች ወይም የማከማቻ ተቋማት አለመዘጋጀት ምክንያት መርከቦች ለቀናት በመቆም የሚከፍሉትን ከፍተኛ የዲመሬጅ ወጪ የሚያስቀር መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በመሆኑም አዲሱ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ መርከቦች እንደደረሱ ነዳጁን በቀጥታ ወደ ማከማቻው እንዲያወርዱና በቧንቧ መስመር ወደ ኢትዮጵያ እንዲጓጓዝ ስለሚያደርግ የትራንስፖርት ቀናትን በከፍተኛ ሁኔታ ያሳጥራል።

ፕሮጀክቱ ሁለት ዋና ዋና የገቢና የኢኮኖሚ ጥቅሞችን የሚያስገኝ ሲሆን፤ የመጀመሪያው ከቧንቧው እና ከነዳጅ ማከማቻው አገልግሎት የሚገኝ ቀጥታ ገቢ ነው።

ሁለተኛው ደግሞ በኢኮኖሚው ውስጥ የናፍጣ፣ የቤንዚንና የሌሎች ነዳጅ ምርቶች የትራንስፖርት ወጪ በመቀነሱ ምክንያት የሚፈጠረው አጠቃላይ የአገልግሎት እና የንግድ ውድድር አቅም ማደግ መሆኑንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ የሀገሪቱን መንግሥት ፍላጎት በመወከል በፕሮጀክቱ ውስጥ ባለድርሻ ሆኖ እንደሚሳተፍ የተገለጸ ሲሆን፣ ፕሮጀክቱ የሀገሪቱን የሎጂስቲክስ አሰራር ከዘመናዊ የትራንስፖርት ሞዴል ጋር ለማጣጣም የሚደረገው ጥረት አካል መሆኑም ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም