ቀጥታ፡

ሕወሓት - “ድመት መንኩሳ ……”



ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ /ሕወሓት/ በዘወትር መደበቂያው በደደቢት በረሃ ውስጥ ተጸንሶ የካቲት 11 ቀን 1967 ዓ.ም ለኢትዮጵያ መከራ ይዞ ተወለደ።የመጀመሪያዎቹ የትግሉ እንቅስቃሴ መስራች ወጣቶች 11 ነበሩ።

ሕወሓት በኢትዮጵያውያን ላይ የተጣባውን የጭቆና ቀንበር ለማስወገድ ተፀንሶ ገንጣይ አስገንጣይ ባንዳ ሆኖ ህልው ሆነ፤ ለዚህም ነው እነ አረጋዊ በርሔ (ዶ/ር) በጊዜ የተገለሉት፤ እነ ገሠሠ አሠፋ /ስሁል በሴራ የተገደሉት። በእርግጥ ድርጅቱ ሲመሰረት ተጋድሎ ሓርነት ሕዝቢ ትግራይ /ተሓሕት የሚል መጠሪያ ነበረው፤ በኋላ የስም እንጂ የግብር ለውጥ ሳያደርግ ወደ ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ /ሕወሓት/ ተቀየረ።

ሕወሓት የኢትዮጵያውያን ጭቆና “ጥራኝ ጫካው” ያስባላቸው ድርጅቶችን በማታለልና በማጭበርበር ከጎኑ በማሰለፍ በ1983 ዓ.ም ወታደራዊውን የደርግ ስርዓት አስወግዶ መንበረ ስልጣኑን ተቆጣጠረ።ታላቋን ትግራይ ለመመስረት ዓላማ አንግቦት የተነሳው ጸረ ኢትዮጵያው ሕወሓት የሚጠላትን ሀገር የሚመራበት ዕድል ከዕጁ ሰተት ብሎ ገባለት።

በ27 ዓመታት የአምባገነንነት የአገዛዝ ዘመኑ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ብቻ በሚያወጧቸው ሪፖርቶች መሰረት በሚመራው ህዝብ ላይ በርካታ ግፎችን የፈጸመ ድርጅት ሆኖ ተመዝግቧል። ሰብዓዊ መብት ጥሰት የዜጎች እስር በገፍ ሆነ።

የፖለቲካና የዲሞክራሲ ምህዳሩን ክርችም አድርጎ በመዝጋቱ ህዝብ አንቅሮ ተፍቶት እያለ የ1997ቱን ምርጫ 99 ነጥብ 6 በመቶ አሸነፍኩ ብሎ የዓለም መሳለቂያነቱን፣ የአምባገነን ቁንጮነቱን፣ ጮሌ ማፍያነቱን በገሀድ አሳይቷል።

የኢትዮጵያን ህዝብ በዘርና በሀይማኖት እየከፋፈለ እስር በርስ በማጋጨት ለዘመናት ተጋምደው በኖሩ ህዝቦች (በተለይም በአማራና ኦሮሞ ህዝቦች) ዘንድ ጥላቻና ቁርሾን እየዘራ ሀገር ጠልነቱን አስመስክሯል። በሜቴክና ኢፈርት በተባሉ ድርጅቶች የራሱን ወታደራዊ አዛዦችና አንጃዎች በማሰማራት የኢትዮጵያን መርከብ ሳይቀር የሚዘርፉ የማፍያ ቡድኖችና ግለሰቦችን ፈጥሯል።

የመከላከያ ሠራዊት እና ሌሎች የጸጥታና ደህንነት ተቋማት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የህዝቦቿን ደህንነት ከማስጠበቅ ይልቅ የወያኔ ፍላጎት ማስፈፀሚያ አንጃዎች ሆነዋል፤ ለ27 ዓመታት በህዝብ ላይ የፈጸመው ግፍ በኢትዮጵያውያን የተባበረ ክንድ በ2010 ዓ.ም ተወግዶ በምትኩ በሀገር በቀል የመደመር እሳቤ የሚመራ በህዝብ የተመረጠ መንግሥት መንበሩን ያዘ።

ከለውጡ በኋላ “እኔ ያልመራኋት ኢትዮጵያ መኖር የለባትም” የሚለው እብሪተኛው ሕወሓት መቀሌ መሽጎ በስልጣን ላይ በነበረበት ዘመን ያደራጀውን የጥፋት ሴል በማሰማራት በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የእርስ በርስ ግጭት በመፍጠር የተጸነሰበትን የጥፋት ዓላማ አስቀጥሏል።

ለዚህም ነው የትግራይ ክልል የቀድሞው ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገብሩ አስራት “ሕወሓት እኔ ብቻ አውቃለሁ፣ የሚል ተቸካይ ሀሳብ ያለው የቁሞ ቀር ግለሰቦች ስብሰብ ነው” የሚሉት።

ዛሬም አብዮታዊ ዲሞክራሲ በተሰኘ “የእውር ድንበር” ፅንሰ ሀሳብ ላይ ተጣብቆ “እኔ ያልመራኋት ሀገር ትፍረስ” የሚል ግትር አቋም እንዳለው የገለጹትን በዋቢነት መጥቀስ ይቻላል።

ሕወሓት ከምስረታው ጀምሮ አምባገነን መሆኑን በማንሳት፤ “በህዝብ ግፊት ከስልጣን ከተወገደ በኋላ አሸባሪነትን ጨምሮ የለየለት ማፍያ ሆኗል” ብለዋል።በፊት የአምባገነንነቱ ማስፈፀሚያ ህግና አሰራር እንደነበረው አስታውሰው፤በአሁኑ ወቅት ህዝብን በማናለብኝነት የሚያንገላታ የፖለቲካ ድርጅት እንኳን መሆን የተሳነው መርህ አልባ ስብስብ መሆኑን ያነሳሉ።

ሕወሓት በትግራይ ሕዝብ ላይ የዘረጋውን ህገ ወጥ ሥርዓት በመጠቀም በዘረፋና ብዝበዛ ላይ ተሰማርቷል፤ ጥቂት ቡድኖች ብቻ ሀብት የሚያከማቹበት፣ ሕዝቡን ለከፋ ረሀብ፣ ስደትና ድህነት የሚዳርግ ሥርዓት ሆኗል ይላሉ።

ይህ አልበቃው ብሎ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. የትግራይ እናቶችን ሰብል ሲሰበስቡ፤ የትግራይ ህፃናትን ትምህርት ቤት ሲገነቡ በዋሉ የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ አባላት ላይ ጥቃት ፈጽሟል።የሀገር ክህደት አውራ የባንዳነት ቁንጮ መሆኑን ደጋግሞ አሳይቷል፤ ዛሬም ክህደት ቤት ሰርቶበታል።

በትግራይ ክልል ህፃናት የብዕር መጨበጫ ጣቶቻቸው የክላሽ ምላጭ እንዲስቡ ተገደዋል፤ ወጣቶች ከትምህርት ገበታ ታፍሰው ራሳቸውን እቶን እሳት ከሚተፋ የጥይት ሀሩር ውስጥ ያገኙታል።ይህ የትግራይ ወጣቶች ዘወትራዊ ልምድ፤ በሕወሓት የተፃፈላቸው እጣ ፋንታ ሆኗል። የወንጀለኞች ቡድን የሆነው የሕወሓት አንጃ የትግራይን እናቶች ያለ ጧሪ አስቀርቷቸዋል።

በሰሜኑ ጦርነት ወቅት ወጣቶችን አስፈጅቶ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ምት ከእርሱ ላይ ሊያርፍበት ሲል ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የድረሱልኝ ጩኸት አሰማ። የወታደራዊ ሀይል መዛባትና የፖለቲካ ህልውነት አደጋ ሲያጋጥመው ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም የፕሪቶሪያን የሰላም ስምምነት ለምኖ ፈርሟል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት የቀድሞዋ አፈ ጉባኤና የስምረት ፓርቲ ምክር ቤት አባል ኬሪያ ኢብራሂም የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት የትግራይ እናቶችና ወጣቶችን የመኖር ተስፋ ያለመለመ፤ ለነገ ህልም አለኝ፣ ሰላም ተፈጥሯል ጥያቄዎች በሰላም ይፈታሉ የሚል ተስፋ ያላቸው ወጣቶችን የፈጠረ፤ የጥይት ድምጽ የጠፋበት መልካም ዕድል ያበሰረ መሆኑን ያስታውሳሉ።

የትግራይ ህዝብና የሕወሓት ፍላጎት የተለያዩ መሆኑን የሚገልጹት ኬሪያ ኢብራሂም፤ ስምምነቱን ሰላም እንደሚያመጣ በመረዳት የደገፈው ህዝቡ ቢሆንም የሕወሓት ቡድን ግን ለጊዜ መግዣ ካባ አድርጎት እንደነበር በመጥቀስ፤ “ስምምነቱን በግልጽ በመጣስ ጦርነት ህልውናው መሆኑን አሳይቷል” ብለዋል።

ጦርነት ልብሱ የህዝብ ሲቃ ጉርሱ የሆነው የሕወሓት አንጃ ለምኖ የፈረመውን የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ገና በጠዋቱ በመጣስ የጦርነት ነጋሪት መጎሰም ጀምሯል።

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የቀድሞ ፕሬዚዳንት ጌታቸው ረዳ፤ የሕወሓት ቡድን አባላት ከስልጣን ውጭ መኖር እችላለሁ ብለው የማያምኑ፤ ከስልጣን የለቀቁ ዕለት ተጠያቂ የሚሆኑበትን ብዙ ወንጀል የሰሩ አሁንም እየሰሩ ያሉ የወንጀል ኢንተርፕራይዞች መሆናቸውን ይናገራሉ።

የትግራይ ህዝብ የሰላም ስምምነቱን ደጋፊ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ጌታቸው፤ ”የፕሪቶሪያው የሰላም ሥምምነት የኮንትሮባንድ ጥቅሜን ያስቀርብኛል ብሎ ያሰበው ቡድን ግን ስምምነቱን በገሃድ ጥሶ ወንጀል ይፈጽማል” ብለዋል።

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሕወሓት ድርብርብ ወንጀል እየፈጸመ መሆኑን ተረድቷል፤ ሊያወግዘውም እንደሚገባ አሳስበዋል። የፌዴራል መንግስት በትግራይ ክልል ሰላም እንዲሰፍን ያሳየው ትዕግስት የሚደገፍ ነው፤ ዋናው የለውጡ ባለቤቶች የትግራይ ወጣቶችና ፖለቲከኞች በመሆናቸው ቡድኑን በጋራ መታገል አለባቸው ብለዋል።

“ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ” እንዲሉ በመቃብር አፋፍ ላይ ሆኖም ግብዓተ መሬቱ እስኪፈጸም የትግራይን ወጣት ለማስጨረስ ቆርጦ ተነስቷል።

የትግራይ ክልል የቀድሞው ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገብሩ አስራት፤ ተስፋ በቆረጠ ሰዓት ያገኘውን የፕሪቶሪያ ሥምምነት እንኳን መተግበር ተስኖት በሥምምነቱ መሰረተ የተቋቋመውን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በመፈንቀል ስልጣን የተቆጣጠረ የሥልጣን ጥመኛ ቡድን መሆኑን አንስተዋል።

“ሰላም ከመጣ በትግራይ ወጣቶችና እናቶች ተጠያቂነት እንደሚኖር ስለሚያውቅ በጦርነትና በትርምስ ውስጥ ብቻ መኖርን መርሁ አድረጎታል” ብለዋል።

የሕወሓት ታጣቂዎች ከባድና ቀላል መሣሪያዎችን ለሀገር መከላከያ ሠራዊት በማስረከብ ወደ ተሀድሶ ገብተው ማህበረሰቡን እንዲቀላቀሉ፤ ተፈናቃዮች እንዲመለሱ የገባውን ውል ለጦርነት አጀንዳው ማስፈጸሚያ ብሎ አንገራገረ፤ ይባስ ብሎ በፌዴራል መንግሥቱና በሕወሓት ሥምምነት የተመሰረተውን ጊዜያዊ አስተዳደር በሀይል በመፈንቀል መንበረ ስልጣኑን ተቆጣጥሮ የራሱን የዘረፋ አንጃ በትግራይ ክልል መንግሥትነት ሰይሟል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት የቀድሞዋ አፈ ጉባኤና የስምረት ፓርቲ ምክር ቤት አባል ኬሪያ ኢብራሂም ወጣቶችን አስገድዶ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ማስገባት በዓለም አቀፍ ህግ ጭምር የተከለከለ ቢሆንም፤ ትምህርት ቤቶችን በመዝጋት ወታደራዊ ማሰልጠኛ ተቋማትን ከፍተው የትግራይን ወጣትና ሀብት የገንዘብ ምንጫቸው አድርገውታል ብለዋል።

በእርግጥም ወጣቶችን በግዳጅ መመልመያ አዋጅ በማውጣት የጭካኔያቸውን ጥግ ለዓለም አሳይተዋል። ለሕወሓት በትግራይ የሚኖር ትግራዋይ “ትግራዋይ” የሚሆነው የእነሱን አስተሳሰብ ከተቀበል ብቻ ነው።ስለሆነም ሁሉም ከትግራይ ህዝብ ጎን በመታገል ጥይት ሳይተኮስ ሰላም ማስፈንና የትግራይ ወጣቶችን ጥያቄ መመለስ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ትናንት ራሱ በለኮሰው እሳት የትግራይን ህዝብ ሲገድልና ሲዘርፍ ከነበረው ጸረ ኢትዮጵያ ሻዕቢያ ጋር በመተባበር ኢትዮጵያን ለማፍረስ “ጽምዶ” የተባለ የጥፋት አደረጃጀት ፈጥሯል። የኢትዮጵያ ዕድገትና ሰላም ከወትሮም የማይዋጥላት ግብጽ የምትጋልበው ፈረስ ሆኗል።

ሕወሓት የኢትዮጵያን አለመረጋጋት እንደ ቋሚ አጀንዳ አድርገው ከሚሰሩ የውጭ አካላት ጋር እየሰራ ነው።ትግራይን ወደ ኋላ ለመመለስ ትግራይ ውስጥ መሰረተ ልማት በማውደም በመዝረፍና ተቋማትን ሆነ ብሎ ካፈረሰው የኤርትራ መንግስት ጋር መተባበር ትልቅ ወንጀል እንደሆነ አስረድተዋል።

“ሕወሓት የሰብዓዊ ጥሰትና የኮንትሮባንድ ህልውናውን የሚያስቀጥልለት ካገኘ የትም ሀገር ይሄዳል” ያሉት አቶ ጌታቸው፤ ከትግራይ ህዝብ ህልውና በላይ ለራሱ ህልውና ቅድሚያ የሚሰጥ ይሉንታ ቢስ ድርጅት መሆኑን ነው የተናገሩት።

በኢትዮጵያዊነቱ የማይደራደረው የትግራይ ህዝብ ይሄንን እኩይ ዓላማ ያነገበ የጥፋት ቡድን በቃህ ሊለው ይገባል።ለኢትየጵያ ዳር ድንበር መከበር ልጆቹን ሲገብር የኖረው የትግራይ ህዝብ ከአብራኩ በወጡ ባንዳዎች ሀገሩን አሳልፎ በመስጠት ከታሪካዊ ጠላቶቹ ጋር ሲዶልት ቆሞ ማየት የለበትም።

አቶ ገብሩ አስራት “ሕወሓት እወክልሀለሁ” የሚለው የትግራይ ህዝብ ላይ ጭፍጨፋና ዘረፋ ከፈጸመው የሻዕቢያ ሀይል ጋር በማበር የትግራይ እናቶችን ለዳግም ሰቆቃ እያዘጋጀ ነው። ከውጭ ሀይሎችና ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በመተባበር የሚፈጽመውን የሀገር ክህደት ወንጀል የትግራይ ህዝብ በጋራ በቃህ ሊለው ይገባል ብለዋል።

በትግራይ ክልል የወጣቶች የግዳጅ ምልምላ ህጋዊ ሆኖ በአዋጅ ወጥቷል። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጭምር ውጉዝ የሆኑ ወንጀሎችን በመፈጸም ጭካኔውን በግላጭ አሳይቷል።በትግራይ ክልል ወጣቶችን በግዳጅ ይመለምላሉ፤ ፈቃደኛ ያልሆኑት ይረሽናሉ። በዚህም አብዛኛው ወጣት የግዳጅ አፈሳውን በመፍራት ከክልሉ ወጥቶ እየተሰደደ ተፈናቃይ ሆኗል፤ በትግራይ ህዝብ ላይም የህልውና አደጋ ደቅነዋል።

“ይህ ወንጀል ነው” ያሉት አቶ ጌታቸው፤ የትግራይ ህዝብ ልዕልና የሚረጋገጠው በሰላም ብቻ እንደሆነ ይናገራሉ።እነዚህን በህገ አራዊት የሚመሩ የሰው ህይወት እንደከንቱ የሚያዩ የጥፋት ቡድኖችን የትግራይ ወጣቶች በቃችሁ ሊሏቸው ይገባል ብለዋል።

ወይዘሮ ኬሪያ እንደሚሉት፤ የሕወሓት ቡድን አጀንዳ አጥፊ መሆኑን በውጭም ሆነ በሀገር ውስጥ ያለው ትግራዋይ ይገነዘባል። መንግስት ለሰላም ያሳየውን ቁርጠኝነት በማድነቅ፤ ቀጣይነት እንዲኖረው ጠይቀዋል።

እኛ ለሰላም ቅድሚያ ስንሰጥ በትግራይ ህዝብ ጥቅም ላይ የምንደራደር ይመስላቸዋል፤ ከጦርነት ኪሳራ እንጂ ትርፍ የለም፤ ሰላም ደግሞ አክስሮ አያውቅም፤ የትግራይ ህዝብም ተገድደው ወደ ሰላማዊ መንገድ እንዲመጡ መታገል አለበት በማለት ነው አፅንኦት የሰጡት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም