ቀጥታ፡

አዲስ መንግሥት፤ የጸናች ኢትዮጵያ

በፖለቲካ ሳይንስ ጽንሰ ሐሳብ፣ የአንድ መንግሥት ጥንካሬ የሚለካው በሕዝብ ዘንድ ባለው የፖለቲካ ቅቡልነት ነው።

ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም የተካሄደው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ከቅቡልነት ጋር እጅጉን ይቆራኛል። በጠቅላላ ምርጫውም ከ54 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ተሳትፎ አድርጓል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰኔ 14 ቀን 2018 ዓ.ም ይፋ ባደረገው የምርጫ ውጤት ብልፅግና ፓርቲ አብላጫ ድምፅ በማግኘት ማሸነፉን ገልጿል።

በድምፅ አሰጣጥ እለትም፤ በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች በነበረው ከፍተኛ የመራጮች ሰልፍና በአንዳንድ አካባቢዎች በነበረው የዝናብ ሁኔታ ምክንያት የድምፅ አሰጣጡ እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ ተራዝሞ የተካሄደበት በኢትዮጵያ የምርጫ ታሪክም አድስ ምዕራፍ የተፈጸመበት ነበር።

ይህ መጠነ ሰፊ የሕዝብ ተሳትፎ መንግሥት ባለፉት ዓመታት ላከናወናቸው ሀገራዊ የልማት፣ የኢኮኖሚና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሥራዎች የሰጠው ትልቅ ዕውቅና ማሳያ ነው።

ዜጎች በምርጫው አሉታዊ ጫናዎችን ሳይበግሯቸው መሳተፋቸው የሀገሪቱን የዴሞክራሲ ባህል ብስለት ወደ ላቀ ደረጃ አሸጋግሮታል።

የምርጫ ሂደቱ ለሀገረ መንግሥት ግንባታ መጠናከር የሚጫወተው ሚናም ቁልፍ የሚባል ነው።

ምርጫው 42 የፖለቲካ ፓርቲዎችና ከ10 ሺህ በላይ ዕጩዎች የተሳተፉበት በመሆኑ፣ የፖለቲካ ኃይሎች ጥያቄዎቻቸውን ከኃይልና ከግጭት ይልቅ በምርጫ ካርድ መፍታት እንደሚገባ የጋራ ስምምነት የፈጠሩበት ሲሆን ይህም ህጋዊ የሀገረ መንግሥት መዋቅርን ያጠናክራል።

የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በኢትዮጵያ የሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደት ላይ ያበረከተው ቀዳሚው አስተዋጽኦ፣ የፖለቲካ ሥልጣን ይዞታን ሙሉ በሙሉ በሕግና በሕዝብ ፍላጎት ማዕቀፍ ውስጥ በማስገባት የመንግሥትን ህጋዊ ቅቡልነት ማሰደጉ ነው።

ከ54 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ተመዝግበው በነቂስ ወጥተው ድምፅ መስጠታቸው፣በዜጋውና በሀገረ መንግሥቱ መካከል ያለውን ማኅበራዊ ውል በከፍተኛ ደረጃ አጠናክሮታል።

ይህ መጠነ ሰፊ ሕዝባዊ ተሳትፎ፣ የሥልጣን ፉክክር ከመሣሪያ ግጭትና ከትጥቅ እንቅስቃሴ ወጥቶ በሰላማዊ የምርጫ ካርድ ውድድር ላይ ብቻ እንዲመሠረት በማድረግ፣ መንግሥት ያለ አስገዳጅ ኃይል በህዝብ ፈቃደኝነት ላይ ብቻ እንዲመሠረት ትልቅ መሰረት የሚጥል ነው።

ምርጫው መንግሥት ካገኘው የስራዎቹ እውቅና በተጨማሪ ህዝቡ ትልቅ አደራ የሰጠበትም ጭምር ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የምርጫ ውጤቱን ተከትሎ በሰጡት አስተያየት የተገኘው ድምፅ ፍጹም መዘናጋትን የሚፈጥር ሳይሆን ለመንግሥት የተሰጠ ታላቅ ህዝባዊ አደራ መሆኑን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳመለከቱት፣ ህዝቡ ጥይትና ማስፈራሪያዎችን ሳይበግሩት በነቂስ ወጥቶ ድምፅ የሰጠው፣ በመንግሥት የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን በላቀ ስኬት እንዲያስቀጥል፣ የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጥ እና በተለይም ሥርዓታዊ ሌብነትንና ሙስናን በቁርጠኝነት እንዲያጠፋ ነው።

ይህ መጠነ-ሰፊ የህዝብ ተሳትፎ ለአዲሱ መንግሥት የማይናወጥ ህጋዊ መሠረትና ከፍተኛ የፖለቲካ ቅቡልነት የሰጠ ሲሆን፣ ኢትዮጵያውያን ለሰላም፣ ለአካታችነትና ለዴሞክራሲያዊ ውድድር ያላቸውን የጸና አቋም ለዓለም ያስመከሩበት መሆኑንም ተናግረዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባወጣው መረጃ መሠረት፤ መስከረም 25 ቀን 2019 ዓ.ም. ለሚከናወነው አዲስ የመንግሥት ምሥረታና የምክር ቤቶች መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት አስፈላጊው ዝግጅት ተጠናቋል።

የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬታማ መሆን የኢትዮጵያን ሀገረ መንግሥት ግንባታ ወደ አዲስና አስተማማኝ ምዕራፍ ያሸጋገረ ክስተት ነው።

የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሂደትና መስከረም 25 ቀን የሚከናወነው አዲሱ የመንግሥት ምሥረታ በሀገሪቱ የፖለቲካ ባህል ውስጥ የተቋማዊ አቅምና የህግ የበላይነት መጎልበትን በተግባር ያሳዩ ናቸው።

ቀጣዮቹ አምስት ዓመታት የተጀመሩትን ስራዎች በተጨባጭ ወደ ላቀ ህዝባዊ ተጠቃሚነትና ብልጽግና የሚቀይርበት ዘመን ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም