ቀጥታ፡

አልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ - የባለ ጥቁር ጋማ አንበሳ መገኛ

ጎብኚዎች ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት ከሚነሳሱባቸው ዋና ዋና ምክንያቶች መካከል ያሏት ጥንታዊና ድንቅ የታሪክ፣ የባህልና የተፈጥሮ ሀብት ስብስቦች እንደሆኑ ዋነኛዎቹ ናቸው።

በዩኔስኮ የተመዘገቡ በርካታ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ታሪካዊ ቅርሶች ባለቤት መሆኗ ፣ የሰው ልጅ መገኛነቷን የሚያረጋግጡ ሳይንሳዊ ግኝቶች፣ እንዲሁም የአረቢካ ቡና የመጀመሪያ መገኛ መሆኗ እና ሌሎችንም መጥቀስ ይቻላል።

“ታሪኳንና ቅርሶቿን ገልጦ ለተመለከተ መልክአ ምድሯን ለቃኘ በማህጸኗ ያቀፈቻቸውን እንስሳት ፣ አዕዋፍና ዕጽዋት ዓይኑን ገልጦ ላሰሰ ፣ የሕዝቦቿን ባህል ፣ ትውፊት ፍልስፍና በማስተዋል ለመረመረ ኢትዮጵያ የመስህቦች ማንጸሪያ የልዩነት አጽናፍ ማስረጃ ናት” …የመደመር መንግሥት መጽሐፍ ገጽ 260

ቱሪዝምን ማሳደግ ሃገራችን ከዘርፉ ልታገኘው የሚገባትን ሰፊ ጥቅም ማረጋገጥ የመደመር መንግስት ትኩረት ካደረገባቸው አምስቱ የኢኮኖሚ ምሰሶዎች አንዱ ነው።

የበርካታ ቱሪስቶችን ቀልበ ከሚስቡትና በተፈጥሮ ፀጋዎች ከታደሉ ሥፍራዎች አንዱ የአልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ በኢትዮጵያ በስነ-ምህዳር ልዩነቱና ለዱር እንስሳት ምቹ በሆነው የተፈጥሮ ሁኔታው የሚታወቅ ነው።

ፓርኩ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በምዕራብ ጎንደር ዞን ቋራ ወረዳ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን፣ በ1998 ዓ.ም በይፋ በብሔራዊ ፓርክነት ተከልሎ ለጎብኚዎች ክፍት ተደርጓል።

የፓርኩ አጠቃላይ የቆዳ ስፋት 3 ሺህ 276 ካሬ ኪሎ ሜትር የሚያካልል ሲሆን፣ ከሱዳን ድንበር ጋር ይገናኛል። ፓርኩ ስሙን ያገኘው አካባቢውን አቋርጦ ከሚያልፈውና ለዱር እንስሳቱ ዋነኛ የውሃ ምንጭ ከሆነው "አልጣሽ" ከተባለው ወንዝ ነው።

ከአዲስ አበባ በስተሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ 1 ሺህ 025 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ይህ ፓርክ፣ ያልተነካ ተፈጥሮንና የዱር እንስሳት ህይወትን ለመመልከት ትልቅ እድልን የሚሰጥ ስፍራ ነው።

የአልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ መልክአ-ምድር በዋናነት ሜዳማና ዝቅተኛ ቦታዎችን ያካተተ ሲሆን ከፍታው ከባህር ጠለል በላይ ከ500 እስከ 900 ሜትር ይደርሳል። የአየር ጠባዩ ሞቃታማና ደረቅ ሲሆን፣ በዋናነት በሳቫና ሳር ምድር፣ በጥቅጥቅ የግራርና የቀርከሃ ደኖች የተሸፈነ ነው።

በፓርኩ ውስጥ የሚያልፉት የአልጣሽና አዩባ ወንዞች በተለይም በደረቁ ወቅት ለዱር እንስሳቱ አስፈላጊውን ውሃ ያቀርባሉ። በተጨማሪም በዝናብ ወቅት የሚፈጠሩ ጊዜያዊ ረግረጎችና የውሃ አካላት ለተለያዩ አእዋፍና የውሃ ውስጥ ህይወት ፍጥረታት ምቹ የመኖሪያ ከባቢን ይፈጥራሉ።

አልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ አልፎ አልፎ የሚታዩና የመጥፋት አደጋ የተደቀነባቸው የዱር እንስሳት መኖሪያም ነው። በፓርኩ ከሚገኙ አጥቢ እንስሳት መካከል አንበሳ፣ ነብር፣ ሳላ፣ አጋዘን፣ ሚዳቋ፣ ጦጣ፣ ዝንጀሮ፣ የዱር አህያና የዱር ውሾች ይጠቀሳሉ። በተለይም በአፍሪካ ብቸኛ የሆነው ባለ ጥቁር ጋማ አንበሳ የሚገኘውም በዚሁ ፓርክ ነው። እ.ኤ.አ. በ2016 የተደረገ ሳይንሳዊ ጥናት እንደጠቆመውም፣ በዛ ያሉ የአንበሳ መንጋዎች በዚህ ፓርክና በአጎራባቹ ይዞታ ውስጥ እንደሚኖሩም ተረጋግጧል።

ከ200 በላይ የሚሆኑ የአገር ውስጥና ከሌሎች ዓለማት (ከአውሮፓና ኤስያ) የሚሰደዱ የአእዋፍ ዝርያዎች በፓርኩ ውስጥ ይገኛሉ። ይህም ፓርኩን ለወፍ አድናቂዎችና ተመልካቾች ተመራጭ ያደርገዋል። በፓርኩ ውስጥ የመድኃኒትነትና የኢኮኖሚ እሴት ያላቸው የተለያዩ የግራር ዝርያዎች፣ የቀርከሃ ጫካዎችና የዕጣን ዛፎች በስፋት ይበቅላሉ።

የአልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ ከሱዳኑ ዲንደር ብሔራዊ ፓርክ ጋር ተጎራባች የሚያደርገው ሰፊ የድንበር ግንኙነትም አለው። ሁለቱ ፓርኮች ተያያዥ በመሆናቸው በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል ድንበር ተሻጋሪ የተፈጥሮ ጥበቃ ቀጣና እንዲፈጠር ምክንያት ሆነዋል። ይህ ግንኙነት የዱር እንስሳቱ ያለ ምንም የወሰን ችግር በነጻነት እንዲንቀሳቀሱና የመራባት ወሰናቸውን እንዲያሰፉ ትልቅ ዕድልን ፈጥሮላቸዋል።

በብሔራዊ ፓርኩ የወሰን ማካለል፣ የጥበቃ አቅምን የማጠናከር፣ የህገ-ወጥ አደን እና የሰደድ እሳት ስጋቶችን የመቀነስ ስራዎች ተሰርተዋል። የአካባቢው ማህበረሰብም ፓርኩን በባለቤትነት እንዲንከባከብና ተጠቃሚም እንዲሆን በንብ ማነብ፣ በእንሰሳት መኖ ልማት እና በአካባቢ ጥበቃ ስራዎች ላይ እንዲሰማራ ለማድረግ የማህበረሰብ ተኮር ፕሮጀክቶች ተቀርፀዋል።

ወደ ፓርኩ የሚያስገቡ የውስጥ ለውስጥ መንገድ መተላለፊያዎችን የማስተካከል፣ የመቆጣጠሪያ ኬላዎችን የመገንባት እና ወደፊት የስነ-ምህዳር ቱሪዝም መስህብ የሚሆኑ ቦታዎችን የመለየት ቅድመ-ዝግጅቶች እየተከናወኑ እንደሚገኙም መረጃዎች ያሳያሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም