ቀጥታ፡

የጤና ተቋማት በራሳቸው የፋይናንስ አቅም የመድሃኒቶች ግዥ የመፈጸም አቅም ጎልብቷል 

አዲስ አበባ ፤ መስከረም 15/2019 (ኢዜአ) ፦የሀገሪቱ የጤና ተቋማት በራሳቸው የውስጥ ገቢ አስፈላጊ የሆኑ መድሃኒቶችና የህክምና ግብዓቶች ግዥ የመፈጸም አቅማቸው እየጎለበተ መምጣቱን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ፋርማሲ ማህበር ለ6ተኛ ጊዜ የዓለም የፋርማሲ ባለሙያዎች ቀንን አክብሯል። በዚሁ ጊዜም የማህበረሰብ ፋርማሲ ላይ ትኩረት ያደረገ የፓናል ውይይት ተካሂዷል።


 

በጤና ሚኒስቴር የሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ በቀለ አሻግሬ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፣ የጤና ተቋማት በራሳቸው የፋይናንስ አቅም መድሃኒቶችና የህክምና ግብዓቶች ግዥ የመፈጸም አቅማቸው እያደገ መጥቷል። 

ለአብነትም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የጤና ተቋማት በራሳቸው በጀት 17 ቢሊዮን ብር ወጪ በማድረግ የመድሃኒት ግዥ መፈጸማቸውን ጠቅሰዋል።

ይህም የአቅርቦት ሂደቱን ወጥ የሚያደርገው መሆኑን ጠቁመው፤ ለዚህ ደግሞ የፋርማሲ ባለሙያዎች ድርሻ ትልቅ መሆኑን አንስተዋል።

ከውጭ የሚገባውን ክትባት በሀገር ውስጥ ለመተካት ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

በመስኩ የሚካሄደው ምርምር፣ ፈጠራ እና የእውቀት ሽግግር ለጤናው ሥርዓት መጠናከር ጉልህ ድርሻ አለው ያሉት አማካሪው፣ በዚህ ረገድ የፋርማሲ ባለሙያዎች አበርክቶ ሊጠናከር እንደሚገባም አስገንዝበዋል። 

በተለይም የመድሃኒቶች የጎንዮሽ ጉዳት ሪፖርት ማድረግ ላይ ያሉ ክፍተቶችን በጥናት ለይቶ መፍትሄ በማመላከት ረገድም የፋርማሲ ባለሙያዎች ተሳትፎ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።

በኢትዮጵያ የእናቶችና ህጻናት ሞት እንዲሁም ተላላፊ በሽታዎች እየቀነሱ መሆኑን የገለጹት አማካሪው፣ ለዚህም የፋርማሲ ባለሙያዎች ድርሻ ትልቅ መሆኑን አንስተዋል። 

የፋርማሲ ባለሙያዎችን ማብቃት እና በቅንጅት መስራት ከተቻለ ትልልቅ ውጤቶችን ማምጣት እንደሚቻል የተገኘው ውጤት ማሳያ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

የአገር ውስጥ መድኃኒት አምራቾች ጥራታቸውንና አቅማቸውን እንዲያሳድጉ የጤና ሚኒስቴር አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።


 

የኢትዮጵያ ፋርማሲ ማህበር ፕሬዝዳንት ዶክተር ዳንኤል ዋቅቶሌ በበኩላቸው፤ የፋርማሲ ባለሙያዎች መድሃኒቶች ለተጠቃሚዎች ሙያዊ በሆነ መንገድ ተደራሽ በማድረግ፣ ለታካሚዎች በሚሰጡት ምክር እንዲሁም በመድሃኒት አስተዳደር ላይ የማይተካ ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል።

ማህበሩ የፋርማሲ ባለሙያዎች ከወቅቱ ጋር የሚራመድ እውቀት እንዲገነቡ የሙያ ላይ ሥልጠናዎችን እየሰጠ ነው ብለዋል።

ከዚህ ባለፈም ማህበሩ በአጠቃላይ ለጤናው ዘርፍ ግብዓት የሚሆኑ ፖሊሲዎች፣ አሰራሮችና ደንቦች ውጤታማ በሆነ መልኩ እንዲዘጋጁም በንቃት በመሳተፍ ሀገራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን አብራርተዋል።

የዘንድሮ የዓለም የፋርማሲ ባለሙያዎች ቀን "የፋርማሲ ባለሙያዎችን ማብቃት ለተሻለ ነገ" በሚል መሪ ሀሳብ በመከበር ላይ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም