በአዳማ ከተማ የመስቀል ደመራ በዓልን በድምቀት ለማክበር የሚያስችል ዝግጅት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
በአዳማ ከተማ የመስቀል ደመራ በዓልን በድምቀት ለማክበር የሚያስችል ዝግጅት ተደርጓል
አዳማ ፤ መስከረም 15/2019 (ኢዜአ) ፦ በአዳማ ከተማ የመስቀል ደመራ በዓልን በድምቀት ለማክበር የሚያስችል ዝግጅት መጠናቀቁን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የምስራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
ዝግጅቱን በማስመልከት የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብፁዕ አቡነ ጎርጎሪዮስ እና የሃይማኖት አባቶች ዛሬ ማምሻውን የደመራ ሥፍራውን ጎብኝተዋል።
የጽሕፈት ቤቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መላከ ሣህል ቀሲስ ነጋሽ ሀብተወልድ ለኢዜአ እንዳስታወቁት፤ የመስቀል ደመራ በዓል ሃይማኖታዊና ብሔራዊ በዓል ነው።
የመስቀል ደመራ በዓል የፍቅር፣ የሰላም፣ የአንድነትና የነፃነት አርማ በመሆኑ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በዓሉን በድምቀትና ባማረ መልኩ ታከብረዋለች ብለዋል።
በዚህ ረገድ በአዳማ ከተማ በነገው ዕለት የመስቀል ደመራ በዓል የሚከበርበትን የመስቀል አደባባይ በከተማው አስተዳደር እና በሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አስተባባሪነት ዛሬ ጠዋት የማጽዳት እና ሌሎችም የቅድመ ዝግጅት ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል።
በደመራ ክብረ በዓል ማክበሪያ ሥፍራ የጽዳት ዘመቻ ላይ የሃይማኖት አባቶችን ጨምሮ ከሰንበት ትምህርት ቤት የተውጣጡ ወጣቶችና በጎ ፈቃደኞች እንዲሁም የከተማ አስተዳደሩ የሥራ ኃላፊዎች ተሳታፊ መሆናቸውን ገልጸዋል።
አዳማ ከተማን ጨምሮ በምሥራቅ ሸዋ ዞን በሚገኙ ሁሉም ወረዳዎችና ከተሞች የመስቀል ደመራ በዓልን ሃይማኖታዊ ትውፊቱን በጠበቀ መልኩ ማክበር የሚያስችል ዝግጅት መጠናቀቁን የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ አረጋግጠዋል።
በዓሉ የአንድነት፣ የፍቅር፣ የይቅርታ፣ የአብሮነት፣ የምሥጋናና የተስፋ እሴቶች የሚገለጹበት ሃይማኖታዊ ክብረ በዓል መሆኑንም አስረድተዋል።
በነገው የአከባበር ሥነ ሥርዓት ላይ ከከተማ አስተዳደሩና ከሁሉም ደብራት የተውጣጡ የሃይማኖት አባቶች፣ የቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪዎች፣ የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች እና የእምነቱ ተከታዮች እንደሚገኙ አውስተዋል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከሚከበሩ ሃይማኖታዊ የአደባባይ በዓላት መካከል አንዱ የመስቀል ደመራ በዓልን ምዕመናን ደመራ ደምረው፣ ችቦ እያበሩ ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን በመጠበቅ ያከብሩታል።