መስቀል የፍቅር፣ የሰላም እና የአንድነት መገለጫ ነው - ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ - ኢዜአ አማርኛ
መስቀል የፍቅር፣ የሰላም እና የአንድነት መገለጫ ነው - ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ
አዲስ አበባ ፤ መስከረም 15/2019 (ኢዜአ) ፦መስቀል የፍቅር፣ የሰላም እና የአንድነት ማሳያ መሆኑን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ እና የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ገለጹ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የተለያዩ የሃይማኖት አባቶች እና የከተማዋ ነዋሪዎች በተገኙበት በመስቀል ደመራ ማክበሪያ ስፍራ የጽዳት መርሃ ግብር ተከናውኗል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ እና የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፣ መስቀል የፍቅር፣ የሰላም እና የአንድነት ትልቅ መገለጫ ነው።
በዛሬው ዕለት የሃይማኖት ተቋማት በጋራ በመሆን በበዓሉ ማክበሪያ ስፍራ የጽዳት መርሀግብር በጋራ ማከናወናቸው ትልቅ አርአያነት ያለው የአንድነት ተግባር መሆኑን አንስተዋል።
በፍቅርና በአንድነት ሆነን በየትኛውም የሃይማኖት በዓል በዚሁ መልኩ ተገናኝተን በጋራ የመስራት ባህላችንን ማጠናከር ይኖርብናልም ብለዋል።
አካባቢን ማጽዳትና ማስዋብ ለሚመጡ እንግዶች አቀባበል ምቹ ሁኔታዎችን እንደሚፈጥር ገልጸው በጽዳት መርሃ-ግብሩ ላይ ለተሳተፉ አካላት ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ቡዜና አልከድር በበኩላቸው ፣ የመስቀል ደመራ በዓል የሃይማኖት ሥርዓት ብቻ ሳይሆን የጋራ ባህል፣ የትብብር፣ የአንድነትና የሰላም መገለጫ ነው ብለዋል።
የመስቀል ደመራ በዓል የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (UNESCO) የማይዳሰስ የሰው ልጅ የዓለም ቅርስ ሆኖ መመዝገቡን አስታውሰው፤ ይህም የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የመላው ዓለም ጭምር የጋራ ሀብት መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።
በመስቀል አደባባይ የተከናወነው መርሃ ግብር ከጽዳት በላይ ትርጉም እንዳለው አመልክተው፤ ይህም የዜግነት ተሳትፎን፣ የጋራ ኃላፊነትንና ለከተማዋ ያለንን ፍቅር የምናሳይበት ተግባር ነው ሲሉም ገልጸዋል።
አዲስ አበባ ፈጣን እድገት ላይ የምትገኝ የባህል፣ የታሪክና የቱሪዝም ማዕከል መሆኗንም ጠቁመዋል።
ወደ ከተማዋ የሚመጡ እንግዶች የሚያዩት የጽዳት፣ የሰላምና የእንግዳ ተቀባይነት እሴት ለሀገር ገጽታ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለውም ተናግረዋል።
ሰላማዊ እና ንጹህ ከተማ የጎብኚዎች ቁጥር እንዲጨምር በማድረግ የሆቴል እና መስተንግዶ፣ የትራንስፖርት፣ የንግድና አገልግሎት ዘርፎችን በማንቀሳቀስ ለዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ጠቁመው፤ ይህም የሀገርን ኢኮኖሚ የማነቃቃትና የማሳደግ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል።
የከተማዋ ነዋሪዎች እንግዶችን በክብር በመቀበል፣ አካባቢን ንጹህ በማድረግ፣ ቅርሶችን በመጠበቅና የበዓላትን ሰላም በማስጠበቅ በኩል ወሳኝ ሚናቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ጽዳት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ገዛኸኝ ዴሲሳ፤ የመስቀል ደመራ በዓል የአብሮነትና የወንድማማችነት መገለጫ ታላቅ የአደባባይ በዓልና በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ እንግዶች የሚታደሙበት በመሆኑ አካባቢን ማስዋብ አስፈላጊ ነው ብለዋል።
የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ምክትል ዋና ጸሐፊ ሼህ አብዱልሃሚድ አህመድ በበኩላቸው፤ የመስቀል ደመራ በዓል የዓለምን ትኩረት የሳበ ትልቅ ሀብት በመሆኑ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ትውፊቱን ጠብቆ እንዲከበር ሁሉም ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ሕብረት የአዲስ አበባ ክልል ዋና ጸሐፊ ፓስተር ሙላት ኤርሚያስ፤ በጽዳት መርሃ ግብሩ መሳተፋቸው በኢትዮጵያ የብዝሃነት እውነታ ውስጥ እርስ በእርስ በመከባበርና በሰላም አብሮ መኖር እንደሚቻል ለማሳየት መሆኑን ተናግረዋል።