ቀጥታ፡

በባሕር ዳር የትምህርት ቤት ምገባ የተማሪዎችን ውጤት በማሻሻል ተጨባጭ ለውጥ አምጥቷል

ባህር ዳር ፤ መስከረም 15/2019 (ኢዜአ) ፦በባሕር ዳር ከተማ እየተካሄደ ያለው የተማሪዎች ምገባ መጠነ ማቋረጥን ከመቀነስ ባለፈ የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ ረገድ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣቱን የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት መምሪያ አስታወቀ።   

የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የምክር ቤት አባላት በከተማዋ የመማር ማስተማር ሥራንና የምገባ እንቅስቃሴን ጎብኝተዋል።


 

የመምሪያው ኃላፊ ሙሉዓለም አቤ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም ተማሪዎች እንዳያረፍዱ፣ እንዳይቀሩና ትምህርት እንዳያቋርጡ በማድረግ በኩል ተጨባጭ ለውጥ አስገኝቷል።

ተማሪዎች ትምህርታቸውን በተገቢው መንገድ እንዲከታተሉ እና ውጤታማ እንዲሆኑ በማድረግ በኩልም ውጤት እየተገኘበት መሆኑን ገልጸዋል።

የምገባ ፕሮግራሙ የትምህርት ጥራት እንዲረጋገጥ በሚደረገው ጥረት እገዛ እያደረገ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በከተማ አስተዳደሩ በያዝነው የትምህርት ዘመን 30 ሺህ ሕፃናትን ለመመገብ ታቅዶ እየተተገበረ ሲሆን፣ እስካሁን በአራት ትምህርት ቤቶች ምገባውን ማስጀመር ተችሏል ብለዋል።

የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ጌትነት እውነቱ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ለተማሪዎች ምገባ ውጤታማነት የሁሉም አካላት ትብብርና ድጋፍ ወሳኝ ነው ብለዋል።


 

ከምገባው በተጨማሪ የትምህርት ጥራትንና ተደራሽነትን ለማሳካት ለመማር ማስተማር ሂደቱ የሚያግዙ ግብዓቶችን የማሟላት ሥራ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም ጠቁመዋል።

ምክር ቤቱ የሕዝብ ውክልናውን በመጠቀም መንግሥትንና ኅብረተሰቡን በማገናኘት እየሠራ ሲሆን፣ በቀጣይም በትምህርት ዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ ክትትልና ድጋፎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።

በከተማዋ የሚገኘው የጠይማ 2ኛ እና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ሙሉጌታ ባለው እንዳሉት፤ በከተማዋ የተጀመረው የተማሪዎች ምገባ ተማሪዎች ትምህርታቸውን በጉጉት እንዲከታተሉ እያደረጋቸው ነው።

አሁንም የተማሪዎች የክፍል ጥምርታ ተመጣጣኝ እንዲሆን በማድረግ በኩል የተጀመሩ የተቀናጁ ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ገልጸዋል።

ከተማ አስተዳደሩ ባለፈው ዓመት ለትምህርት ቤት ምገባ 69 ሚሊዮን ብር ወጪ ማድረጉንም ጠቅሰዋል።

በከተማዋ በሚገኙ 250 ትምህርት ቤቶች 187 ሺህ ተማሪዎችን መዝግቦ ለማስተማር እየተሠራ ሲሆን፣ እስካሁን በተደረገ ጥረት 94 በመቶ ማሳካት እንደተቻለም አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም