ጣና- የውበት ፈርጥ፣ የሀገር ጌጥ - ኢዜአ አማርኛ
ጣና- የውበት ፈርጥ፣ የሀገር ጌጥ
ባህር ዳር ፤ መስከረም 15/2019 (ኢዜአ) ፦ጣና- የውበት ፈርጥ፣ የሀገር ጌጥ
የተፈጥሮ፣ የታሪክ፣ የባህልና የስልጣኔ መገለጫዎች ያሏት ኢትዮጵያ የሁሉ መገኛ፣ ምቹ መኖሪያና ተመራጭ የቱሪስቶች መዳረሻ ሀገር መሆኗ ይታወቃል። የተራሮች ውበት የፏፏቴዎች ድምቀት የአራት ወቅቶች ፍርርቅ የሚመላለስባት በተፈጥሮ የታደለች ሀገርም ናት። ከጥንታዊ ቤተ መንግሥቶቿ እስከ ገዳማቷ፣ ከተፈጥሯዊ ውበቶቿ እስከ ዘመናዊ የከተማ ልማቶቿ በስፋት እየተሰራባት ተጨባጭ ውጤትም እየተመዘገበባት ይገኛል።
በኢትዮጵያ ትልቁ ሐይቅ ጣና፤ የአባይ ውሃ የህልውና መሰረት፤ የጣና ሐይቅ ውበት የሚገለጥበት ባህር ዳር እና አካባቢው ከሃብትም ባለፈ የታሪክ፣ የባህል፣ የብዝሃ ሕይወት፣ የኢኮኖሚና የቱሪዝም መሰረትም ነው።
ከዚሁ በመነሳትም የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የጣና ሐይቅን እና አካባቢውን የባዮስፌር ሪዘርቭ በማለት መዝግቦታል። በጣና ሃይቅ ላይ የሚገኙት ደሴቶችና ልዩ ልዩ ገዳማትም የሃይማኖት፣ የታሪክና የባህል መሰረቶች ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ።
የጣና ገዳማት የኢትዮጵያን መንፈሳዊና ሥነ-ጥበባዊ ታሪክ የሚያስተላልፉ ሕያው ማህደሮች ሲሆኑ በገዳማቱ የቆዩ መጻሕፍት፣ የሃይማኖት ጥበብ ሥራዎችና ታሪካዊ ቁሳቁሶች ይገኛሉ። በመሆኑም የውበት ፈርጥ፣ የሀገር ጌጥ የሆነው ጣና እና ገዳማቱ ከቱሪዝም መስህብነት ያለፈ ትርጉም ያለቸው የሀገር ሃብቶች ናቸው።
የጣና የቱሪዝም እድገት ከውሃ መጓጓዣ ጋር በቀጥታ የተያያዘ በመሆኑ የውሃ ላይ የትራንስፖርት አማራጮችን ግዙፏን ጣና ነሽ 2 እና ሌሎችም ዘመናዊ ጀልባዎችን ወደ ስራ በማስገባት ለቱሪስቶች ምቹ ሁኔታ መፍጠር አስችሏል።
ለጉብኝት ወደ ባህር ዳር የሚያቀኑ ሁሉ ከጣና ሃይቅ ጋር ተሰናስሎ የተገነባውን የኮሪደር ልማት በማድነቅ በዘመናዊ ጀልባዎች ተሳፍረው ጎርጎራን፣ ገዳማቱንና ሌሎችንም የቱሪዝም መስህቦች በቀላሉ መጎብኘት እየቻሉ ነው።
በመሆኑም በጣና ውበት የተቀረጸች፣ በተፈጥሮና በታሪክ ሃብቶች የታደለችው ባህር ዳር ከተማ በእድገትና ማንሰራራት ላይ ትገኛለች። የባህር ዳር የኮሪደር ልማትም ከጣና ሐይቅና ማራኪ ውበቱ፣ ከገዳማቱና ዓለም አቀፍ ደረጃውን ጠብቆ የተገነባው የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት ጋር ተሰናስሎ አስደናቂ የመስህብ ስፍራ ሆኗል። ከአካባቢው ከመልክአ ምድር እና ከጣና ሃይቅ ጋር በተናበበ መልኩ ደረጃውን ጠብቆ የተገነባው የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት የቱሪስቶች ምቹና ተመራጭ መዳረሻ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።
የባህር ዳር ከተማ የኮሪደር ልማት ከአካባቢው የተፈጥሮ ሃብት ጋር ተሰናስሎ ምቹ መዝናኛዎች፣ ዘመናዊ ጀልባዎች፣ የእግርና የሳይክል መጓጓዣዎች ተጨምረውበት ባህር ዳርን ይበልጥ ውብና ማራኪ አድርጓታል። ለጉብኝት ወደ ባህር ዳር የሚያቀኑ ቱሪስቶችም ጣናን አይተው፣ ገዳማቱን ጎብኝተው፣ ጎርጎራ ላይ ተዝናንተው ቆይታቸውን አራዝመው ይመለሳሉ።