በክልሉ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎችን በማልማትና በማስተዋወቅ ዘርፉን ለማነቃቃት እየተቻለ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎችን በማልማትና በማስተዋወቅ ዘርፉን ለማነቃቃት እየተቻለ ነው
ደሴ፤ መስከረም 15/2019 (ኢዜአ) ፦በአማራ ክልል የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎችን በማልማትና በማስተዋወቅ ዘርፉን ለማነቃቃት እየተቻለ መሆኑን የክልሉ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ገለጸ።
የደሴ ከተማ አስተዳደር "ዲጂታል አጀንዳና ሰው ሰራሽ አስተውሎት ለቱሪዝም አዲስ ቅኝት" በሚል መሪ ቃል የዓለም የቱሪዝም ቀንን በፓናል ውይይት አክብሯል።
በዚሁ ወቅት የቢሮው ምክትል ኃላፊ አየለ አናውጤ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ በክልሉ ያለውን እምቅ የቱሪዝም ሀብት አልምቶ ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችሉ ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው።
ባለፉት ዓመታት የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማልማት፣ በማስተዋወቅና ንቅናቄ በመፍጠር ረገድ አበረታች ውጤቶች ለማስመዝገብ በመቻሉ ተግባሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
ለዚህም አገልግሎቱን ከዲጂታል ቴክኖሎጂ ጋር በማስተሳሰር ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊና ሃይማኖታዊ የቱሪስት መዳረሻዎችን በተሻለ መንገድ ለማልማት እንደሚሰራ ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም የቱሪዝም ሀብቶችን በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ለማስመዝገብ በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
በተያዘው በጀት ዓመትም የተለያዩ ቅርሶችንና የቱሪስት መዳረሻዎችን በማልማትና በመጠገን ወደ አገልግሎት ለማስገባት የታቀደ መሆኑን ገልጸዋል።
የደሴ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ በበኩላቸው፤ በከተማው የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎች በተሻለ መንገድ ለጎብኝዎች ምቹ እየተደረጉ መሆኑን አስረድተዋል።
ይህም የአካባቢውን የአብሮነት፣ የመቻቻል፣ የፍቅርና የአንድነት ባህል ከማስተዋወቅ ባለፈ፣ ለወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠርና ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ገልጸዋል።
በደሴ ከተማ ሁለት ቤተ መንግሥቶች፣ ሙዚየምና ሌሎችም የቱሪስት መዳረሻዎች መኖራቸውን የጠቀሱት ደግሞ የደሴ ከተማ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሰይድ አራጋው ናቸው።
አገልግሎቱን በቴክኖሎጂ በመደገፍ የቱሪስቶችን ቆይታ ከማራዘም ባሻገር ሀብቱን ለትውልድ ለማስተላለፍ የተከናወኑ ተግባራት ውጤት የተገኘባቸው መሆኑንም አብራርተዋል።
በወሎ ዩኒቨርሲቲ የቱሪዝምና ሆቴል ማኔጅመንት ትምህርት ክፍል መምህር አስናቀው አትሉግ በበኩላቸው፤ የዓለም የቱሪዝም ቀን ሲከበር ዘርፉን በአዲስ መንገድ ለመቃኘትና ለማልማት ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል።
በአሁኑ ወቅት የቱሪዝም እንቅስቃሴ በዲጂታል ቴክኖሎጂ እየተመራ መሆኑን ጠቁመው፣ አሰራሩን ዘመናዊ በማድረግ ዘርፉን ለማነቃቃት የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አመላክተዋል።
በፓናል ውይይቱ ላይ የክልል፣ የደሴ ከተማና የአጎራባች ዞኖችና ከተሞች አመራሮች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።