ቀጥታ፡

ቡና እና ሰላም አትጡ!

ጅማ፣ መስከረም 15/2019 (ኢዜአ)፡-ቡና እና ሰላም አትጡ!  - "Bunaaf nagaa hindhabinaa" 

ስለ ጅማ ሲነሳ ቡና እና ሰላም ሁልጊዜም አብረው የሚጠሩ ህያው እሴቶች ናቸው። በምናብ ለሚያስባትም ሆነ ደርሶ  የተመለከታት ሁሉ እንደሚያረጋግጠው፣ ጅማ የመዓዛማው ቡናዋ መፍለቂያ ብቻ ሳትሆን፤ የአረንጓዴ ተፈጥሮዋን ውበትና የሰላሟን ሙቀት ለእንግዶቿ የምታድል ልዩ ከተማ ናት። 

የጅማ ከተማ ታሪካዊ እሴቷን ጠብቃ ወደፊት በሚያራምዳት የልማት ጉዞ ላይ ትገኛለች። ከተማዋ በየዕለቱ አዲስ ገጽታ በመላበስ ላይ ስትሆን፣ ሰፊ የከተማ ገጽታዋ፣ ንጹሕ አየሯና አረንጓዴ ውበቷ የሚያልፉ እንግዶችን ሁሉ በልዩ ሁኔታ በመሳብ ላይ ይገኛሉ። ዛሬ ጅማ ይበልጥ ማራኪና ውብ እየሆነች መጥታለች። ታሪካዊ ቅርሷንና ማንነቷን እንደጠበቀች ወደ አዲስ ምዕራፍ እየተሸጋገረች የምትገኘው ይህች ከተማ፤ እውነትም ጅማ ሆናለች።


 

የኮሪደር ልማት ለጅማ ከተማ አዲስ ህይወትና ማራኪ ውበት ሰጥቷታል። በአረንጓዴ ስፍራዎቿና በንጹህ አየሯ ጎብኚዎችን በመሳብ ላይ የምትገኘው ይህች ከተማ፣ በልማቱ አማካኝነት ለበርካታ ወጣቶች የኑሮ መሠረት የሚሆን የሥራ ዕድል ፈጥራለች። የተቀየሩት ጎዳናዎቿና በዙሪያቸው የደማመቁት የንግድ እንቅስቃሴዎቿ ደግሞ ጅማን ወደፊት የመራመድ ጉዞ ቁልጭ አድርገው ያሳያሉ።

በጅማ እየተከናወነ ያለው የዘመናዊ መንገዶች ግንባታ ለከተማዋ አዲስ ህይወት ከመስጠቱም በላይ፣ የማኅበረሰቡን የቆየ የመሠረተ ልማት ጥያቄ በመመለስ የኑሮ ዘይቤን እያቀለለ ይገኛል። ይህ የተሻሻለ የመንገድ ዝርጋታ ከተማዋን ምቹና ተደራሽ በማድረግ የባለሃብቶችን ትኩረት በመሳብ ላይ ሲሆን፣ ጅማንም የክልሉ የኢንቨስትመንትና የንግድ ማዕከል የማድረግ ራዕይን እውን እያደረገ ነው።

አዌቱ ወንዝ ዛሬ የጅማ ከተማ አዲስ የውበትና የሰላም ማዕከል ሆኗል። ከተማዋን የበለጠ ማራኪ ያደረገው ይህ የወንዝ ዳርቻ ልማት፣ ቀደም ሲል ማኅበረሰቡን ስጋት ላይ ይጥል የነበረውን የጎርፍ አደጋ በማስቀረት የነዋሪዎችን ስጋት አስወግዷል። ይህም የከተማ ልማት ውበትን ከማስፈን ባለፈ የሕዝብን ደኅንነትና ምቾት የታደገ ተግባራዊ አርአያነቱን አረጋግጧል።


 

የታሪክና የባህል ማዕከል የሆነችው ጅማ፤ በቡና መዓዛዋ ብቻ ሳይሆን በድንቅ የእንጨት ቅርጻ ቅርጽ ጥበቧም የብዙዎች ትኩረት ስባለች። የዚህች ውብ ከተማ እንግዳ የሆነ ሁሉ ተፈጥሯዊ ውበቷን ብቻ አይቶ አይመለስም፤ የጅማን መዓዛማ ቡና ቀምሶ፣ የጥበብ ባለሙያዎችን እጅ ሥራ የሆኑ ውብ የእንጨት ቅርጾችን በመታሰቢያነት በመያዝ የከተማዋን ሕያው ታሪክ ይዞ ይጓዛል።

የታሪክና የተፈጥሮ ውህደት ማሳያ የሆነችው ጅማ፤ የንጉሥ አባ ጅፋር ቤተመንግሥት እድሳትና የቦዬ ሐይቅ ልማት ተደምረው አዲስ የቱሪዝም ምዕራፍ ከፍተውላታል። በቦዬ ሐይቅ ዙሪያ የተከናወነው አስደናቂ ለውጥ የአካባቢውን የተፈጥሮ ህይወት ያላቀ ሲሆን፣ ለአካባቢው ነዋሪዎችና ለከተማዋ እንግዶች ተመራጭና ጥሩ ትዝታ የሚያስቀር የመዝናኛ መዳረሻ ሆኗል።

ጅማ ታሪኳንና ማንነቷን ጠብቃ በከፍተኛ ፍጥነት በመልማት፣ በመገንባትና በማደግ ላይ ትገኛለች። ከተማዋ የቀድሞውን ታሪካዊ ትውስታ ከአዲሱ የከተማ ገጽታ ጋር በማዋሃድ፣ በታሪክና በዘመናዊነት መካከል ጥንካሬ ያለው አዲስ ድልድይ በመገንባት ላይ ናት።


 

ከዚህ ባሻገር ጅማ ማራኪ የኮንፈረንስ ማዕከል እየሆነችም መጥታለች። ትልልቅ ሆቴሎች ተገንብተዋል፤ የተለያዩ ትልልቅ ሁነቶችንም እያስተናገደች ትገኛለች። ይህም ከተማዋን ለጎብኚዎች፣ ለቢዝነስ ሰዎችና ለተለያዩ ተቋማት ሳቢ መዳረሻ እያደረጋት ነው።

ዛሬ ጅማ በዓመት ከ300 ሺህ በላይ ዜጎች የሚጎበኟት ከተማ ሆናለች። የሚመጡትም የከተማዋን ውበት ለማየት ብቻ ሳይሆን፣ ታሪኳን ለመዳሰስ፣ ቡናዋን ለመቅመስ፣ ተፈጥሯዊ ጸጋዋን ለመለማመድና የጅማን ልዩ ማንነት ለመረዳት ነው።


 

ጅማ ታሪኳን ጠብቃ፣ ውበቷን አስጠብቃ ወደፊት እየተራመደች ነው። አረንጓዴው ውበቷ፣ የአዌቱ ወንዝ ፍሰት፣ የቦዬ ሐይቅ ገጽታ፣ የአባ ጅፋር ቤተ መንግስትና ታሪክ እንዲሁም የቡና ሽታዋ ተደምረው ለከተማዋ የራሷን ልዩ ቀለም ሰጥተዋታል።

ቡናዋን ጠጥቶ ሰላሟን ያየ እንግዳም የጅማን ትዝታ ይዞ ይመለሳል።

ኑ ቡና ጠጡ የሚለውን የጅማዎች የቆየ ግብዣ ተከትሎ "Bunaaf nagaa hindhabinaa" - ቡና እና ሰላም አትጡም ከጅማዎችና እንግዶቿ አፍ  ስምም ፈጥሮ ይኖራል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም