አዲስ የሚመሰረተው መንግሥት ሜጋ ፕሮጀክቶችንና የልማት ተግባራትን አጠናክሮ ማስቀጠል ይጠበቅበታል - ኢዜአ አማርኛ
አዲስ የሚመሰረተው መንግሥት ሜጋ ፕሮጀክቶችንና የልማት ተግባራትን አጠናክሮ ማስቀጠል ይጠበቅበታል
አዲስ አበባ ፤ መስከረም 15/2019 (ኢዜአ) ፦ አዲስ የሚመሰረተው መንግሥት የዜጎችን ተጠቃሚነት ይበልጥ የሚያረጋግጡ ሜጋ ፕሮጀክቶች አጠናክሮ መቀጠል እንደሚጠበቅበት የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አሕመድ ሁሴን ገለጹ።
የአዲሱ መንግሥት ምሥረታና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መክፈቻ ሥነ ሥርዓት መስከረም 25 ቀን 2019 ዓ.ም እንደሚካሄድ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስታውቋል።
በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ከ50 ሚሊዮን በላይ መራጮች ድምጻቸውን በመስጠት ለሀገር ይጠቅማል ያሉትን የፖለቲካ ፓርቲ በመምረጥ ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ያላቸውን ጽኑ መሻት በተግባር አሳይተዋል።
ምርጫው በተሳካ ሁኔታ እንዲካሄድ ያደረገው የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በገለጸው ውጤት መሰረት ህዝቡ ይበጀኛል ይጠቅመኛል በማለት አብላጫ ድምጽ የሰጠው ብልፅግና ፓርቲ መንግስት መመስረት የሚያስችለውን ይሁንታ ማግኘቱን ማሳወቁም ይታወቃል፡፡
የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትንና የክልሎች ምክር ቤቶችን መቀመጫ እንዲያገኙ ድምጽ ሰጥቷቸዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን የረጅም ዘመን የሀገረ መንግሥት ግንባታ ልምድ ያላቸው፣ ለሰላም፣ ለፍትህና ርትዕ ቀናኢ እይታ ያላቸው ህዝቦች መሆናቸውንም አስመስክረዋል።
የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት አሕመድ ሁሴን ለኢዜአ እንዳሉት፤ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ህዝቡ ዴሞክራሲያዊ መብቱን በነጻነት በመጠቀም ለሀገር ይጠቅማል ብሎ ያመነበትን ፓርቲ የመረጠበት ነው።
መንግሥት መመስረት የሚያስችለውን ድምጽ ያገኘው ፓርቲ በርካታ ሀገራዊ ኃላፊነቶችን የሚቀበልበት፣ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ለህዝቡ ይጠቅማል ብሎ ለገባው ቃል ተግባራዊነት የሚተጋበት ጊዜ መሆኑንም ገልጸዋል።
አዲስ የሚመሰረተው መንግሥት የዜጎችን የመልማትና ፍትሐዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ጠንካራና ሉዓላዊነቷ የተጠበቀች ሀገር የመገንባት ኃላፊነት እንዳለበት አንስተዋል።
መንግሥት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር የጀመራቸውን ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች አጠናክሮ እንዲቀጥል ይጠበቃል ብለዋል።
የማዳበሪያ ፋብሪካ፣ የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ፣ የ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ቤቶች ልማትና ሌሎችንም ሜጋ ፕሮጀክቶች ለማሳካት የተጀመረውን ሪፎርም አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ተናግረዋል።
አዲስ መንግሥት በአንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋሉ የጸጥታ ችግሮችን በዘላቂነት መፍታት እንደሚጠበቅበት ገልፀው፤ ሰላም የአንድ ሀገር የልማትና የዕድገት መሠረት መሆኑንም አስረድተዋል።
በሀገራዊ ምክክር ጉባዔው የተመከረባቸው ሀገራዊ ጉዳዮችን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ውይይትና ንግግር ባህል ሆኖ እንዲቀጥል የመሪነት ሚናውን መወጣት እንዳለበትም ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም በማስፈንና ልማትን በማረጋገጥ ረገድ ከሚመሰረተው መንግሥት ብዙ እንደሚጠበቅ ገልጸው፤ ህዝቡ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችና ሌሎችም ተቋማት የሰላም አጋርነት ሚናቸውን መወጣት አለባቸው ብለዋል።