ለትውልዱ የብልጽግና መሠረት እየጣለች ያለች ሀገር፡ ኢትዮጵያ - ኢዜአ አማርኛ
ለትውልዱ የብልጽግና መሠረት እየጣለች ያለች ሀገር፡ ኢትዮጵያ
ኢትዮጵያ ታላላቅ ሀሳቦችን ወደ መሬት በማውረድ የነገዋን የበለጸገች ሀገር ለመገንባት የምታደርገው ጥረት ከዕለት ወደ ዕለት ይበልጥ እየተጠናከረ መጥቷል።
የሀገሪቱ የልማት ምዕራፎች የዕለት ተዕለት ችግሮችን ከመቅረፍ ባለፈ ዘላቂና አስተማማኝ የኢኮኖሚ መሠረት የሚጥሉ ስትራቴጂካዊ ውጥኖችን ተፈጻሚ ማድረግ ላይ ያተኮሩ ናቸው።
ትናንት የነበሩ የሎጂስቲክስ ማነቆዎችን በመስበር የኢነርጂ ደህንነትን የሚያረጋግጡ እና ቀጣናዊ ትስስርን የሚያጠናክሩ ዘመናዊ መሠረተ ልማቶችን በቁርጠኝነት በመገንባት የሀገርን መፃኢ ጊዜ የተቃና ከሚያደርጉ ተግባራት መካከል የሚጠቀስ ነው።
የዛሬ ኢንቨስትመንቶች ነገ ለሚፈጠረው የኢንዱስትሪ፣ የግብርና እና የንግድ አውታር አስተማማኝ ዋስትና የሚሆኑ ናቸው።
በዚህ አውድ ውስጥ በጅቡቲ ዳመርጆግ እና በኢትዮጵያ ደወሌ መካከል የሚዘረጋው አዲስ የነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧ መስመር ፕሮጀክት ትልቅ የሚባል ታሪካዊ ውሳኔ ነው።
የነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧ መስመር ፕሮጀክት የመሠረት ድንጋይ ማስቀመጥ ሥነ ሥርዓቱ ትናንት በጅቡቲ ተካሄዷል።
በሥነ ሥርዓቱ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ታድመዋል።
ፕሮጀክቱ በሁለቱም ጫፎች ላይ በሚገነቡ የማከማቻ ተርሚናሎች የተደገፈ ሲሆን፤ ይህ ታሪካዊ መሠረተ ልማት በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ እና በዳንጎቴ ግሩፕ ጥምረት የሚተገበር መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
ይህ የኢነርጂ መሠረተ ልማት ፕሮጀክት ሀገሪቱ ለዓመታት ስትጋፈጠው የነበረውን የትራንስፖርት መዘግየት እና ውስን የማጠራቀሚያ አቅም በዘላቂነት የሚፈታ እጅግ ወሳኝ እርምጃ ነው ብለዋል።
መልክአ ምድሩ ለሁለቱ ሀገራት የሰጠው የጋራ ኮሪደር ጅቡቲን ከሰፊ ገበያ፣ ኢትዮጵያን ደግሞ ወደ ዓለም አቀፍ ንግድ የሚያገናኝ ቋሚ ድልድይ እንደሆነ ተናግረዋል።
ዛሬ አዲስ አበባ የሚገባ እያንዳንዱ ሊትር ነዳጅ በቦቴ መኪናዎች አምስት ቀናትን አሳልፎ የሚመጣበትን አስቸጋሪ ሂደት አዲሱ የቧንቧ መስመር ወደ አንድ ቀን ገደማ ዝቅ እንደሚያደርገው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።
በጅቡቲ፣ በኢትዮጵያ እና በዳንጎቴ ግሩፕ የጋራ ትብብር የሚዘረጋው ይህ 120 ኪሎ ሜትር የሚረዝም የነዳጅ ቧንቧ መስመር የሎጂስቲክስ ማነቆዎችን ሙሉ በሙሉ የሚቀርፍ ነው።
በሁለቱም ወገኖች ከአንድ ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር በላይ የሚሆን የጋራ ማከማቻ ቦታ የሚዘጋጅ ሲሆን፣ ይህም ዓለም አቀፍ ቀውሶች ሲያጋጥሙ የኢነርጂ አቅርቦቱ እንዳይስተጓጎል ትልቅ ዋስትና የሚሰጥ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው ላይ አንስተዋል።
የተጣራ ነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧ መስመሩ የአፍሪካውያን የትብብር መንፈስ የገለጠ ፓን-አፍሪካዊ ፕሮጀክት መሆኑን ፕሬዝዳንት ኢስማኤል ኦማር ጊሌ ገልጸዋል። ይህ ኢንቨስትመንት የአፍሪካ መንግሥታትና የግሉ ዘርፍ ሲተባበሩ አህጉሪቱ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ መሆን እንደምትችል የሚያሳይ ግልጽ ማሳያ ነው ብለዋል።
ከአፍሪካ ግዙፍ ኢኮኖሚ ያላት ኢትዮጵያ የኢነርጂ፣ ሎጂስቲክስ እና የኢንዱስትሪ አቅሟን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያጠናከረች ትገኛለች።
የዳንጎቴ ግሩፕ መሥራችና ናይጄሪያዊው ባለሀብት አሊኮ ዳንጎቴ እንደገለጹት ኢትዮጵያ ከነበረው በቦቴ ትራንስፖርት የማጓጓዝ በመላቀቅ ደህንነቱ የተጠበቀ፣ ፈጣን እና ቀልጣፋ የነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧ መዘርጋቷ ታላቅ የኢኮኖሚ ድል ነው።
ይህ የተቀናጀ ሥርዓት የምርት ጥራት ቁጥጥርን በማሻሻል እንደ ኢንዱስትሪ፣ አቪዬሽን፣ ትራንስፖርት፣ ግብርና እና ኮንስትራክሽን ያሉት ቁልፍ ዘርፎች በዘላቂነት እንዲደገፉ ያደርጋል።
በጣም ታላቁና ሊሰመርበት የሚገባው ነጥብ ይህ ፕሮጀክት ሙሉ በሙሉ በአፍሪካዊ ካፒታል እና በወጣት አፍሪካውያን መሐንዲሶች የሚገነባ መሆኑ ነው።
ይህ ሁኔታ አፍሪካ የራሷን የልማት ችግሮች በራሷ ዕውቀትና አቅም መፍታት እንደምትችል ትልቅ ማሳያ በመሆን ለአህጉሪቱ ምዕራፍ ይከፍታል።
በዚህ መሠረተ ልማት ግንባታ ላይ የተሳተፉ አካላት ቅንጅት የጋራ እምነትን እና ጽኑ አቋምን ያሳያል። ጅቡቲ መሠረተ ልማቶቿን በማዘመን፣ የኢኮኖሚ አማራጮቿን በማስፋት እና ለቀጣናዊ መረጋጋት አስተማማኝ አጋር ሆና መቀጠሏን አረጋግጣለች።
ይህ ሁሉ ጥረት የሚያሳየው ኢትዮጵያ ለዛሬው ትውልድ ብቻ ሳይሆን ለነገዋ የበለጸገች ሀገር ቋሚ መሠረት እየጣለች መሆኑን ነው።
የነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧ መስመር ፕሮጀክት ትውልዱ በራሱ አቅም ተማምኖ ነገን በእርግጠኝነት መገንባት እንደሚችል የሚያበስር ታላቅ የድል ምዕራፍ ነው።