ቀጥታ፡

የመስቀል ደመራ በዓል አንድነትንና አብሮነትን ይበልጥ ለማጠናከር ጉልህ ሚና አለው

አዲስ አበባ፣መስከረም 15/2019 (ኢዜአ)፦የመስቀል ደመራ በዓል አንድነትንና አብሮነት ለማጠናከር እንዲሁም የወል እሴቶች እንዲጎለብቱ ከፍተኛ ሚና እንዳለው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህልና ኪነ-ጥበብ ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አዲሱ ሻንቆ (ዶ/ር) ገለጹ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህልና ኪነ ጥበብ ቢሮ የመስቀል ደመራ በዓልን ምክንያት በማድረግ “መስቀል ደመራ ቅርሳችን፤ ለሀገራዊ መግባባትና ለወል እሴቶቻችን ግንባታ” በሚል መሪ ሃሳብ የፓናል ውይይት በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡

በውይይቱ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ባህልና ኪነ-ጥበብ ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አዲሱ ሻንቆ (ዶ/ር)፤ የመስቀል ደመራ በኢትዮጵያ ረጅም ታሪክ ያለው፣ ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊና ማኅበራዊ እሴቶችን አጣጥሞ የያዘ ታላቅ በዓል መሆኑን ገልጸዋል።

በዓሉ ፍቅር፣ አብሮነት፣ ወንድማማችነትና አንድነትን የሚያጎለብት መሆኑን የጠቆሙት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፤ የጋራ እሴቶችን ጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ በማስተላለፍ ረገድም የማይተካ ሚና እንዳለው አስረድተዋል። 

አክለውም የመስቀል ደመራ ከሃይማኖታዊ ይዘቱ ባሻገር የኢትዮጵያ አገራዊ መገለጫና የታላቅ ቱሪዝም ምንጭ መሆኑን አንስተዋል።

በዓሉ በከተማዋ በደማቅ ሁኔታ እንዲከበር በከተማ አስተዳደሩ ደረጃ ሰፊ ዝግጅት መደረጉን ጠቅሰው፤ ለአደባባይ በዓላት ምቹ የሆኑ የከተማ መሠረተ ልማቶችና አደባባዮች መገንባታቸው ህዝቡ ባህሉንና እሴቶቹን በጋራ እንዲያከብር አወንታዊ ሁኔታ መፍጠሩን ተናግረዋል።

የመስቀል ደመራ የእምነቱ ተከታዮች፣ ሁሉም የከተማው ነዋሪዎችና ከተለያዩ የዓለም አቀፍና ሀገር ውስጥ የሚመጡ እንግዶች በጋራ የሚሳተፉበት በዓል መሆኑንም ጠቁመዋል።

በመሆኑም በዓሉ ከሃይማኖታዊ ይዘቱ ጎን ለጎን አንድነትን፣ ህብረትንና መፋቀርን ለማጠናከር ያለውን አጋጣሚ በመጠቀም በጋራ ማክበር ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የሚጠበቅ ኃላፊነት መሆኑን አስገንዝበዋል። 

ቢሮው እንደ ተቋም ሃይማኖታዊና ባህላዊ ይዘት ያላቸው የህዝብ በዓላት በሚገባቸው ደረጃ እንዲከበሩ፣ በህብረተሰቡ ዘንድ እንዲሰረጹና ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፉ ማድረግ ከተሰጡት ዋና ዋና ተግባራት መካከል አንዱ መሆኑን ገልጸዋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም