የኮሪደር ልማት ከተሞች ለኑሮ ምቹ፣ ዘመናዊ እንዲሁም የብልጽግና ማሳያ እንዲሆኑ አድርጓል - ኢዜአ አማርኛ
የኮሪደር ልማት ከተሞች ለኑሮ ምቹ፣ ዘመናዊ እንዲሁም የብልጽግና ማሳያ እንዲሆኑ አድርጓል
አዲስ አበባ፤ መስከረም 15/2019 (ኢዜአ):-የኮሪደር ልማት ሥራዎች ከተሞች ለኑሮ ምቹ፣ ውብ፣ ዘመናዊ እንዲሁም የብልጽግና ማሳያ እንዲሆኑ ማድረጉን በከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የፖሊሲና ስትራቴጂ ጥናት ምርምር መሪ ስራ አስፈጻሚ አማን አሰፋ (ዶ/ር) ገለጹ።
በአዲስ አበባ ከተማ የተጀመረው የኮሪደር ልማት፣ አሁን ላይ ወደ ሁሉም የክልል ከተሞች በመስፋፋት አገር አቀፍ የከተሞች ትራንስፎርሜሽን ማዕበል ፈጥሯል።
ይህ የልማት እንቅስቃሴ በሁሉም አቅጣጫ የከተሞችን ገጽታ በመቀየር አስደማሚ የውበትና የዘመናዊነት ለውጥ እያመጣ ይገኛል።
ከተሞችን ለነዋሪዎቻቸው ምቹ፣ ማራኪ፣ አረንጓዴና ስማርት በማድረግ ረገድ በጠንካራ መሰረት ላይ በተገነባ ዘመናዊ ስርዓት እንዲተካ ያደረገ ሲሆን የህዝቡን የአኗኗር ዘይቤ ከማሻሻሉም በላይ ለኢኮኖሚ ዕድገት አዲስ ህይወት በመዝራት የኢትዮጵያን የብልጽግና ጉዞ የሚያፋጥን ድንቅ ክስተት ሆኗል፡፡
በከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የፖሊሲና ስትራቴጂ ጥናት ምርምር መሪ ስራ አስፈጻሚ አማን አሰፋ (ዶ/ር) ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ፈጣን የከተሞች ዕድገት እያስመዘገቡ ካሉ ሀገራት አንዷ ናት።
ተግባራዊ የተደረገው አዲሱ የከተማ ፖሊሲ ከተሞች ለኑሮ ምቹ፣ ዘመናዊና ማራኪ እንዲሆኑ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አብራርተዋል።
የሰዎች የመንቀሳቀስ ምቾት፣ የአረንጓዴ ስፍራዎች ተደራሽነት፣ ለሥራና ንግድ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩ እንዲሁም የመሠረተ ልማት አቅርቦት መሟላቱ የዘመናዊ ከተማ ጥራት መለኪያዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በአሁኑ ወቅት በበርካታ የሀገሪቱ ከተሞች እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት የዜጎችን የአኗኗር ዘይቤ ከማሻሻል ባለፈ፣ የትራፊክ መጨናነቅን በመቀነስ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴውን በእጅጉ እያፋጠነው ይገኛል ብለዋል።
በተጨማሪም አረንጓዴ ስፍራዎችን በማስፋፋት ዜጎች ንጹህ አየርና መዝናኛ እንዲያገኙ ማስቻሉ ከተሞች ውብና ስማርት እንዲሆኑ አድርጓቸዋል ብለዋል።
የአፍሪካ መዲና የሆነችውን አዲስ አበባን ዘመናዊና ስማርት ሲቲ ለማድረግ የተከናወነው የኮሪደር ልማት ሥራ ለሌሎች የክልል ከተሞች አርዓያ መሆን መቻሉን አስገንዝበዋል።
በዚህም በክልል ከተሞችን ተግባራዊ የተደረገው የኮሪደር ልማት የዜጎችን የአኗኗር ዘይቤ የቀየረ፣ የንግድ እንቅስቃሴ እንዲሳለጥ ያደረገ፣ ውበትን የገለጠና ለኢንቨስትመንት ምቹ እንዲሆኑ ያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
የከተማ ኮሪደር ልማት ከተሞችን ውብ፣ ዘመናዊና ለስራ ምቹ በማድረግ አዲስ አገራዊ የመሰረተ ልማት ምዕራፍ የከፈተ ድንቅ ስኬት የከፈተ ሲሆን የልማት እንቅስቃሴ አገራዊ የብልጽግና ጉዞን በማፋጠን ባለፈ፣ ለገጠር ኮሪደር ልማት ዘላቂ ትግበራ ጽኑ መሰረት መጣሉንም ነው የጠቆሙት፡፡