ቀጥታ፡

የመስቀል ደመራ በዓል የአብሮነት፣ የፍቅርና የእንግዳ ተቀባይነት እሴቶች ጎልተው የሚታዩበት ነው

አዲስ አበባ፣መስከረም 15/2019 (ኢዜአ)፦የመስቀል ደመራ በዓል ከሃይማኖታዊ ትውፊቱ ባሻገር የአብሮነት፣ የፍቅርና የእንግዳ ተቀባይነት እሴቶች ጎልተው የሚታዩበት መሆኑን የሃይማኖት አባቶች ገለፁ።

በአዲስ አበባ የተገነቡት መሰረተ ልማቶች ለበዓሉ ልዩ ድምቀት እንደፈጠሩም ተናግረዋል።

የሃይማኖት አባቶቹ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የመስቀል ደመራ በዓል በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት(ዩኔስኮ) የተመዘገበ የዓለም አቀፍ የጋራ ቅርስ በመሆኑ፣ በበዓሉ ወቅት የሚታዩት የአብሮነት፣ የፍቅር፣ የሰላምና የመተሳሰብና የእንግዳ ተቀባይነት እሴቶች ጎልተው የሚታይበት ነው።

የልደታ፣ ቂርቆስና አዲስ ከተማ ክፍለ ከተሞች ቤተ ክህነት ስራ አስኪያጅ ሊቀ ሊቃውንት አባ ጥዑመልሳን አዳነ ቆሞስ እንደገለጹት፣ የመስቀል በዓል በዩኔስኮ ደረጃ ተመዝግቦ በጋራ የሚከበር የህዝቦች የጋራ ሀብት ነው።

ምዕመናን በዓሉን ለማክበር ወደ አደባባይ ሲወጡ ፍቅርን መተሳሰሰብን እና ሀገራዊ አንድነትን በልባቸው ሰንቀው ሊሆን እንደሚገባም አስገንዝበዋል።  

ለበዓሉ ከተለያዩ የዓለም ሀገራትና ከእህት አብያተ ክርስቲያናት የሚመጡ እንግዶችንና የሃይማኖት አባቶችን በኢትዮጵያዊ ባህል፣ በትህትናና በፍቅር መቀበል የሀገርን መልካም ገጽታ ለማሳየት ትልቅ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።  


 

የደብረ ይባቤ ቅዱስ ያሬድ ቤተክርስቲያን ዋና አስተዳዳሪ መላከ ገነት ዘማሪያም ሙጬ በበኩላቸው፤ የመስቀል በዓል ዓለም የዳነበት፣ የሰላም፣ የፍቅርና የአንድነት መገለጫ መሆኑን ተናግረዋል። 

በዘንደሮው የ2019 ዓ.ም የመስቀል በዓል አከባበር ወቅት የአዲስ አበባ ከተማ የኮሪደር ልማትና የወንዝ ዳርቻዎች ገጽታ መለወጥ በዓሉን ልዩ እንደሚያደርገው ገልጸዋል።


 

የማህደረ ስብሃት ቅድስት ልደታ ለማርያም እና ደብረ መድኃኒት መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን ዋና አስተዳዳሪ መላከ ስብሃት ቆሞስ አባ ገብረስላሴ አማረ በበኩላቸው፤  በዓሉ ለሀገር ገጽታ ግንባታ የራሱ ሚና እንዳለው ጠቁመው፤ የመስቀል ደመራ በዓል የአብሮነት፣ የፍቅርና የእንግዳ ተቀባይነት እሴቶች ጎልተው የሚታዩበት መሆኑ ተናግረዋል።  

በአዲስ አበባ የተገነቡት የኮሪደር ልማት የወንዝ ዳርቻ ልማት ስራዎች የከተማዋን ገጽታ እጅግ ውብ ያደረጉት በመሆኑ፣ የበዓሉን ድምቀት እንደሚያጎላው ጨምረው ገልጸዋል። 


 

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የየካ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስኪያጅ መላከ ምህረት በቃሉ ወርቅነህ፤ የመስቀል በዓል የሃይማኖቱ ተከታዮች ብቻ ሳይሆን የሁሉም ኢትዮጵያውያን የጋራ እሴትና ሀገራዊ ሀብት መሆኑን ገልጸው፤ በዓሉ የአብሮነት፣ የፍቅርና የእንግዳ ተቀባይነት እሴቶች ጎልተው የሚታዩበት መሆኑን ተናግረዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም