የመደወላቡ ዩኒቨርሲቲ የቱሪዝም ዘርፉን በጥናትና ምርምር የመደገፍ ተግባሩን ያጠናክራል - ኢዜአ አማርኛ
የመደወላቡ ዩኒቨርሲቲ የቱሪዝም ዘርፉን በጥናትና ምርምር የመደገፍ ተግባሩን ያጠናክራል
ሮቤ፤ መስከረም 15/2018 (ኢዜአ)፦የመደወላቡ ዩኒቨርሲቲ የቱሪዝም ዘርፍን በጥናትና ምርምር የመደገፍ ተግባሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ብርሃነ መስቀል ጠና (ዶ/ር) ገለጹ።
ዩኒቨርሲቲው በዘርፉ የሚያካሂዳቸው የጥናትና ምርምር ተግባራት የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን የሚያነቃቁና ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግሩ መሆናቸው ተመላክቷል።
የመደወላቡ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ብርሃነ መስቀል ጠና (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት መንግስት የቱሪዝም መስህቦችን ለማልማት የሰጠው ትኩረት የቱሪስቶችን ቆይታ በማራዘምና ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ በማሳደግ ረገድ ወሳኝ ሚና እየተጫወተ ነው።
ዩኒቨርሲቲው የሚገኝበት ባሌና አከባቢው ለቱሪዝም ዘርፍ ትልቅ አቅም ያለው በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው ዘርፉን በጥናትና ምርምር የመደገፍ ተግባር እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
እንዲሁም አካባቢው በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፈላጊ የሆኑ የብዝሃ ሕይወትና የታሪካዊ ቅርሶች መገኛ በመሆኑ፤ ዩኒቨርሲቲው ጸጋዎቹን ተደራሽ ለማድረግም ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ሰፊ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።
በባሌ፣ ምሥራቅ ባሌና ምዕራብ አርሲ ዞኖች የሚገኙት የሶፍ ኡመር ዋሻ፣ ድሬ ሼህ ሁሴን እና የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ለቱሪዝም ዘርፉ እድገት ትልቅ አቅም መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
''አንድ ፓርክ ብዙ ዓለም'' በመባል የሚታወቀው የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክና ሌሎች በአካባቢው የሚገኙ መስህቦች ይበልጥ እንዲተዋወቁና እንዲለሙ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ዩኒቨርሲቲው የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑንም ተናግረዋል።
በድሬ ሼህ ሁሴን የመስህብ ስፍራ አካባቢ የሚታዩ ተግዳሮቶች ተፈተው ቅርሱ ይበልጥ እንዲለማ ለማስቻል በዩኒቨርሲቲው ምሁራን እየተከናወኑ የሚገኙ የምርምር ፕሮጀክቶች የዚሁ ጥረት አካል መሆናቸውን አመልክተዋል።
የዩኒቨርሲቲው ምሁራን ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ባለፉት ዓመታት ባደረጉት ጥናት፣ በአካባቢው ከዚህ በፊት በስፋት የማይታወቁ ከ100 የሚበልጡ የቱሪስት መስህቦችና ዋሻዎች በሳይንሱ ዓለም እንዲተዋወቁና እንዲሰነዱ ተደርጓል ብለዋል።
በተጨማሪም መስህቦቹ ያሉበት ቦታ በቀላሉ እንዲለዩ የሚያግዝ የዲጂታል ካርታ የተሰራላቸው መሆኑን ፕሬዝዳንቱ ጠቁመዋል።
በሀገሪቱ የቱሪዝም መዳረሻዎችና ሆቴሎች እየተስፋፉ መሆናቸውን የጠቆሙት ብርሃነመስቀል (ዶ/ር)፤ ዩኒቨርሲቲው ይህን በማደግ ላይ ያለ ኢንዱስትሪ የሚመጥኑ ብቁ ባለሙያዎችን ለማፍራት የተለያዩ ተግባራትን እየተገበረ መሆኑን ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲው በቅርቡ "የቱሪዝምና መስተንግዶ ትምህርትን በሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ማዕቀፍ መቃኘት" በሚል መሪ ሀሳብ ያዘጋጀው ዓለም አቀፍ የምርምር ኮንፈረንስ የዘርፉን ቀጠናዊ ትስስር በማጠናከር በቴክኖሎጂ ለመደገፍ ትልቅ ድርሻ እንዳለው አመልክተዋል።
መድረኩ ዩኒቨርሲቲው መስህቦችን ይበልጥ ለማልማትና ለማስተዋወቅ እያደረገ ላለው ዘላቂ ጥረት ዓለም አቀፍ ተሞክሮ የተገኘበት መሆኑንም ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲው በቱሪዝም ዘርፉ የሚታዩ ተግዳሮቶችንና መልካም አማራጮችን በምርምር በመለየት፣ ዘርፉን ለማሻገርና ቀጣይነት ያለው የቱሪዝም ልማት ለማረጋገጥ የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ፕሬዝዳንቱ አስታውቀዋል።