ቀጥታ፡

የመስቀል ደመራ ከሀይማኖታዊ በዓልነቱ ባሻገር የሰላም፣ የአንድነትና የኢኮኖሚ እድገት አቅምና የጋራ ሀብት ነው- አፈ ጉባዔ ቡዜና አልከድር

አዲስ አበባ፤ መስከረም 15/2019 (ኢዜአ):- የመስቀል ደመራ ከሀይማኖታዊ በዓልነቱ ባሻገር የሰላም፣ የአንድነትና የኢኮኖሚ እድገት አቅምና የጋራ ሀብት ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አፈ ጉባዔ ቡዜና አልከድር ገለጹ። 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ የተለያዩ የሃይማኖት አባቶችና የከተማዋ ነዋሪዎች በተገኙበት በመስቀል ደመራ ማክበሪያ ስፍራ የጽዳት ንቅናቄ መርሃ ግብር ተከናውኗል።


 

አፈ ጉባዔ ቡዜና በመርሃ ግብሩ ላይ እንደገለጹት፣ የመስቀል ደመራ በዓል የሃይማኖት ሥርዓት ብቻ ሳይሆን የጋራ ባህል፣ የትብብር፣ የአንድነትና የሰላም መገለጫ ነው።

የመስቀል ደመራ በዓል የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (UNESCO) የማይዳሰስ የሰው ልጅ የዓለም ቅርስ ሆኖ መመዝገቡን አስታውሰው፤ ይህም የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የመላው ዓለም ጭምር የጋራ ሀብት መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል። 

በመስቀል አደባባይ የተከናወነው መርሃ ግብር ከጽዳት በላይ ትርጉም እንዳለው አመልክተው፤ ይህም የዜግነት ተሳትፎን፣ የጋራ ኃላፊነትንና ለከተማዋ ያለንን ፍቅር የምናሳይበት ተግባር ነው ብለዋል።

አዲስ አበባ ፈጣን እድገት ላይ የምትገኝ የባህል፣ የታሪክና የቱሪዝም ማዕከል መሆኗንም ጠቁመዋል።

ወደ ከተማዋ የሚመጡ እንግዶች የሚያዩት የጽዳት፣ የሰላምና የእንግዳ ተቀባይነት እሴት ለሀገር ገጽታ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል። 


 

ሰላማዊና ንጹህ ከተማ የጎብኚዎችን ቁጥር በመጨመር የሆቴል፣ የምግብ፣ የመጓጓዣ፣ የንግድና አገልግሎት ዘርፎችን በማንቀሳቀስ ለዜጎች የስራ እድል እንደሚፈጥር ጠቁመው፤ ይህም የሀገርን ኢኮኖሚ የማነቃቃትና የማሳደግ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል።   

የከተማዋ ነዋሪዎች እንግዶችን በክብር በመቀበል፣ አካባቢን ንጹህ በማድረግ፣ ቅርሶችን በመጠበቅና የበዓላትን ሰላም በማስጠበቅ በኩል ወሳኝ ሚናቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም