የአፍሪካ ዋንጫ መስራቾቹን ኢትዮጵያ እና ሱዳን ያገናኘው የማጣሪያ ጨዋታ - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ ዋንጫ መስራቾቹን ኢትዮጵያ እና ሱዳን ያገናኘው የማጣሪያ ጨዋታ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 15/2019 (ኢዜአ)፦ በ36ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የምድብ 10 የመጀመሪያ ጨዋታውን ከሱዳን ጋር ዛሬ ጨዋታዋን ያደርጋል።
የሁለቱ ሀገራት ጨዋታ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ በጁባ ብሔራዊ ስታዲየም ይካሄዳል።
በአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ከሱዳንና ሴኔጋል ጋር ለሚደረጉት የማጣሪያ ጨዋታዎች ከአንድ ወር በላይ በሀገር ቤት ዝግጅቱን አድርጓል።
አሰልጣኝ ዮሐንስ በመጀመሪያ ዙር ለ39 ተጫዋቾች ጥሪ ካደረጉ በኋላ በዝግጅት ሂደት የመጨረሻ ስብስቡን ወደ 23 ዝቅ አድርገዋል።
ቡድኑ በሀገር ቤት ቆይታው ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን፣ ከሀዋሳ ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የአቋም መለኪያ ጨዋታዎችን አከናውኗል።
ዋልያዎቹ ከሱዳን ጋር ላለባቸው ጨዋታ ማክሰኞ መስከረም 12 ቀን 2019 ዓ.ም ጁባ ገብተው ዝግጅታቸውን ሲያደርጉ ቆይተዋል።
በ66 ዓመቱ ጋናዊ ጀምስ ክዌሲ አፒያ የሚመራው የሱዳን ብሔራዊ ቡድን 33 ተጫዋቾን በመያዝ ለሁለት ሳምንት ገደማ ለጨዋታው ዝግጅቱን ሲያደርግ ቆይቷል።
ብሔራዊ ቡድኑ መጀመሪያ ዝግጅቱን ሳዑዲ አረቢያ ላይ ካካሄደ በኋላ ቀሪውን የዝግጅት ጊዜ ወደ ደቡብ ሱዳን በማምራት አከናውኗል።
ኢትዮጵያ እና ሱዳን በአፍሪካ እግር ኳስ ውስጥ ትልቅ የታሪክ አሻራ ያላቸው ሀገራት ናቸው።
ሁለቱ ሀገራት እ.አ.አ በ1957 ለመጀመሪያ ጊዜ በሱዳን በተካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ተሳትፎ አድርገዋል።
በዛው ዓመት የተመሰረተው የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) መስራች አባል ሀገራትም ነበሩ።
እ.አ.አ በ1956 ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም አቀፍ የወዳጅነት ጨዋታ ተገናኝተው ኢትዮጵያ 2 ለ 1 አሸንፋለች።
እ.አ.አ በ1959 በግብጽ አስተናጋጅነት በተካሄደው ሁለተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ያደረጉት ጨዋታ ተገናኝተው ነበር።
በወቅቱ ሱዳን 1 ለ 0 አሸንፋለች።
ለ70 ዓመታት በዘለቀው የሁለቱ ሀገራት ፉክክር ውስጥ 41 ጊዜ በውድድርና በወዳጅነት ጨዋታዎች ተገናኝተዋል።
በነዚህ ጨዋታዎች ሱዳን 16 ጊዜ ድል ሲቀናት ኢትዮጵያ በ14ቱ ጨዋታዎች አሸንፋለች። በቀሪ 11 ጨዋታዎች አቻ ተለያየተዋል።
ኢትዮጵያ በነዚህ 41 ጨዋታዎች ላይ 59 ግቦችን ስታስቆጥር ሱዳን 57 ጎሎችን ከመረብ ላይ አሳርፋለች።
ሁለቱ ሀገራት ለመጨረሻ ጊዜ የተገናኙት እ.አ.አ በ2022 ነበር።
በአበበ በቂላ ስታዲየም በተካሄደው የወዳጅነት ጨዋታ ሁለት አቻ ተለያይተዋል።
በአፍሪካ እግር ኳስ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ስፍራ የሚሰጣቸው ሀገራት የሚያደርጉት ጨዋታ ትኩረትን ስቧል።
ኢትዮጵያ ሁለተኛ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዋን ማክሰኞ መስከረም 19 ቀን 2019 ዓ.ም ከሴኔጋል ጋር ታደርጋለች።
36ኛው የአፍሪካ ዋንጫ እ.አ.አ በ2027 በኬንያ፣ ዩጋንዳ እና ታንዛንያ ጣምራ አዘጋጅነት ይካሄዳል።
አህጉራዊው ውድድር ከሰኔ 12 እስከ ሐምሌ 10 ቀን 2019 ዓ.ም በሶስቱ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት በሚገኙ ሰባት ስታዲየሞች ይካሄዳል።
በውድድሩ ላይ 24 ሀገራት ይሳተፋሉ።
ቀሪ ወደ አፍሪካ ዋንጫው የሚያልፉ 21 ሀገራት በማጣሪያ ጨዋታዎች ይለያሉ። በዚህም 48 ሀገራት በ12 ምድቦች ተከፍለው ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።