በአዲስ አበባ ከተማ የሞተር ብስክሌት ማሽከርከር ላልተወሰነ ጊዜ ተከለከለ - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባ ከተማ የሞተር ብስክሌት ማሽከርከር ላልተወሰነ ጊዜ ተከለከለ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 15/2019 (ኢዜአ) ፦ የአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ከዛሬ ከመስከረም 15 ቀን 2019 ዓ.ም ጀምሮ ባለ ሁለት እግር ሞተር ብስክሌት በአዲስ አበባ ማሽከርከር መከልከሉን አስታውቋል።
አንዳንድ ወንጀል ፈጻሚዎች ሞተር ብስክሌትን በመጠቀም የቅሚያ እና የስርቆት ወንጀል ሲፈጽሙ ተይዘው ምርመራ እየተጣራባቸው እንደሚገኝም የአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ገልጿል።
ወንጀል ፈጻሚዎች ከቦታ ቦታ ለመዘዋወር እና የተሰረቁ እቃዎችን ለማጓጓዝ ሞተር ብስክሌትን በብዛት እንደሚጠቀሙም አመልክቷል፡፡
ቁጥራቸው ቀላል የማይባል የሞተር ብስክሌት አሽከርካሪዎች የትራፊክ ደንቡን እንደማያከብሩም ገልጿል።
በተለይም ቀይ መብራትን መጣስ፣ ሌሎች ተሽከርካሪዎችን በመግጨት ማምለጥ፣ ሄልሜት ሳያደርጉ ማሽከርከር፣ የተፋፋቀ እና ለእይታ አስቸጋሪ የሆኑ የሠሌዳ ቁጥሮችን መጠቀም በአሽከርካሪዎቹ በስፋት የሚስተዋሉ የደንብ ጥሰቶች መሆናቸውን ፖሊስ ገልጿል።
ወንጀልን ለመከላከል እና በሞተር ብስክሌት አሽከርካሪዎች የሚፈጸምን የደንብ ጥሰት ለመቆጣጠር ከዛሬ ከመስከረም 15 ቀን 2019 ዓ.ም ጀምሮ ከኮድ 4 እና ከፖሊስ ሞተር ብስክሌት ውጭ ባለ ሁለት እግር ሞተር ብስክሌት ማሽከርከር መከልከሉ ተገልጿል፡፡
የሞተር ብስክሌት አሽከርካሪዎች እና ባለ ንብረቶች አስፈላጊውን እንዲፈጽሙ ያሳሰበው ፖሊስ ይሄንን በሚተላለፉት ላይ ሕጋዊ ርምጃ እንደሚወስድም አስታውቋል፡