ቀጥታ፡

ከአፍሪካ የግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤቶች አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ የኢነርጂ፣ ሎጅስቲክስና የኢንዱስትሪ አቅሟን እያጠናከረች ነው- አሊኮ ዳንጎቴ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 14/2019 (ኢዜአ):- አፍሪካ ውስጥ ካሉት የግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤቶች አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ የኢነርጂ፣ የሎጂስቲክስና የኢንዱስትሪ አቅሟን እያጠናከረች ትገኛለች ሲሉ ናይጄሪያዊው ባለሀብትና የዳንጎቴ ግሩፕ መስራችና ዋና ስራ አስፈጻሚ አሊኮ ዳንጎቴ ገለጹ።

አሊኮ ዳንጎቴ በጅቡቲ ዳመርጆግ እና በኢትዮጵያ ደወሌ መካከል የሚዘረጋው የ120 ኪሎ ሜትር የነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧ እና የ400 ሚሊዮን ሊትር ማከማቻ ተርሚናል ግንባታ ፕሮጀክት ይፋ መደረጉን ገልጸዋል።




በምሥራቅ አፍሪካ ፈጣን ዕድገት እያስመዘገበች ያለችው ኢትዮጵያ  የኢነርጂ፣ የትራንስፖርት፣ የሎጂስቲክስ እና የኢንዱስትሪ ግብዓቶች ፍላጎቷ ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ የሚገኝና ትልቅ ኢኮኖሚ ያላት ሀገር መሆኗን ዳንጎቴ አመልክተዋል።

የዳንጎቴ ግሩፕ በኢትዮጵያ ውስጥ ሰፊ ኢንቨስትመንቶችን እያከናወነ መሆኑን የገለጹት ዳንጎቴ፣ ሀገሪቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ማዳበሪያን ጨምሮ ሌሎች ወሳኝ ምርቶችን ከውጭ በማስገባት ፈንታ ለውጭ ገበያ ማቅረብ እንደምትጀምር ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ከነባረው የከባድ መኪና የትራንስፖርት ጫና በመላቀቅ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ፣ ፈጣን እና ቀልጣፋ የነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧ መስመር አጠቃቀም በመዘርጋት ጠንካራ የኢነርጂ ዋስትናን በዚህ ፕሮጀክት ታረጋግጣለች ብለዋል።

ይህ የኢንቨስትመንት ማዕቀፍ ለኢትዮጵያ የሎጂስቲክስ ማነቆዎችን በእጅጉ እንደሚቀንስ፣ የምርት ጥራት ቁጥጥርን እንደሚያሻሽል እና እንደ ኢንዱስትሪ፣ አቪዬሽን፣ ትራንስፖርት፣ ግብርናና ኮንስትራክሽን ያሉ ቁልፍ ዘርፎችን በዘላቂነት እንደሚደግፍ ነው ያብራሩት።

 



ፕሮጀክቱ ሙሉ በሙሉ በአፍሪካዊ ካፒታል እና በወጣት አፍሪካውያን መሐንዲሶች የሚገነባ መሆኑን የገለጹት ዳንጎቴ፣ ይህም አፍሪካ የራሷን የልማት ችግሮች በራሷ አቅም መፍታት እንደምትችል ትልቅ ማሳያ መሆኑን አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ እና ጅቡቲ በመልክዐ ምድር፣ በጋራ ራዕይ እና በእጣ ፈንታ የተሳሰሩ መሆናቸውን ጠቅሰው የጅቡቲ ኮሪደር የሁለቱንም ሀገራት የንግድ እና የኢኮኖሚ ልውውጥ በማስተሳሰር ረገድ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል።

አፍሪካ ከዕምቅ አቅም ባሻገር ወደ ተጨባጭ ምርት ልትሸጋገር እንደሚገባና በሌሎች ጥገኝነት የመሆን ሁኔታ ሊያበቃ ይገባል ብለዋል።

በዚህ ረገድም አፍሪካ የኢነርጂ ዋስትናን ማረጋገጥ እና በራሷ አቅም መጠቀም እንዳለባት ተናግረዋል።

የአፍሪካ ኤክስፖርት-ኢምፖርት ባንክ (አፍሪ ኤግዚም ባንክ) እና የአፍሪካ ፋይናንስ ኮርፖሬሽን (ኤ.ኤፍ.ሲ) የመሳሰሉ አህጉራዊ የፋይናንስ ተቋማት ለዚህ ታላቅ ፕሮጀክት እያደረጉት ያለው ድጋፍ የአፍሪካን የገንዘብ አቅም የሚያሳይ ነው ብለዋል።

ይህ ታሪካዊ የኢነርጂ መሠረተ ልማት ፕሮጀክት በወቅቱ፣ በጥራት እና በከፍተኛ ዓለም አቀፍ ደረጃዎች ተጠናቆ የሁለቱን አገራት ሕዝቦች እና የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና የኢኮኖሚ ትስስር ለረጅም ዓመታት እንዲያገለግል ጥሪ ማቅረባቸውን ዳንጎቴ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም