ቀጥታ፡

የተጣራ ነዳጅ ማስተላለፊያ ቱቦ መስመሩ ፓን-አፍሪካዊ ፕሮጀክት ነው - የጅቡቲ ፕሬዝዳንት ኢስማኤል ኦመር ጊሌ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 14/2019 (ኢዜአ):- የተጣራ ነዳጅ ማስተላለፊያ የቱቦ መስመር የአፍሪካውያን የትብብር መንፈስ የገለጠ ፓን-አፍሪካዊ ፕሮጀክት መሆኑን የጅቡቲ ፕሬዝዳንት ኢስማኤል ኦመር ጊሌ ገለጹ።

በጅቡቲ ዳመርጆግን ከኢትዮጵያ ደወሌ የሚያገናኝ እና ታላቅ ስትራቴጂካዊ ኢንቨስትመንት የሆነውን አዲስ የተጣራ ነዳጅ ማስተላለፊያ ቱቦ መስመር ዝርጋታ ዛሬ ይፋ ሆኗል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በፕሮጀክቱ መሠረተ ድንጋይ የማስቀመጥ ሥነ-ሥርዓት ላይ ታድመዋል።

የጅቡቲ ፕሬዝዳንት ኢስማኤል ኦመር ጊሌ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ መገኘት በኢትዮጵያ እና በጅቡቲ መካከል ያለውን ጥልቅ እምነት እና የጋራ ጽኑ አቋም የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህ ኢንቨስትመንት የአፍሪካ መንግሥታትና የግሉ ዘርፍ ሲተባበሩ አፍሪካ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ መሆን እንደምትችል የሚያሳይ ፓን-አፍሪካዊ ፕሮጀክት መሆኑን አመልክተዋል።

ፕሮጀክቱ ከ375 ሺህ ኪዩቢክ ሜትር በላይ የሚሆን የነዳጅ ማከማቻ ተርሚናል እንደሚኖረው እና በዓመት 5 ሚሊዮን ቶን ምርቶችን በማስተናገድ የትራፊክ ማነቆዎችን እንደሚፈታ ተናግረዋል።

አፍሪካ ጥሬ ዕቃዎችን እየላከች የተጣራ ነዳጅ በውድ ዋጋ የመግዛት አዙሪት እና ጥገኝነት አሁን ሊጠናቀቅ እንደሚገባና እውነተኛ ነፃነት የሚገኘው በኢነርጂ ራስን በመቻል መሆኑን ነው የገለጹት።

እርስ በእርስ ያልተሳሰሩ መሰረተ ልማቶች ድንበር ተሻጋሪ አይደሉም ያሉት ፕሬዝዳንቱ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና የደነገገውን ህጋዊ ማዕቀፍ በተጨባጭ መሠረተ ልማት መደገፍ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ እምቅ አቅም እና የጅቡቲ ወደቦች ሲቀናጅ የላቀ ስኬት ማስመዝገብ እንደሚቻል አመልክተዋል።

ፕሮጀክቱ በአፍሪካዊ የካፒታል ወጪ የተገነባ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ቴክኖሎጂውንና እውቀቱን ይዘው የሚሠሩት አፍሪካዊ መሐንዲሶችና ወጣቶች መሆናቸው ትልቅ እምርታ መሆኑን ነው የተናገሩት።

ጅቡቲ መሠረተ ልማቶቿን በማዘመን፣ የኢኮኖሚ አማራጮቿን በማስፋት እና ለቀጣናዊ መረጋጋት አስተማማኝ አጋር ሆና እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።

ፕሬዝዳንቱ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ ለአሊኮ ዳንጎቴ፣ ለጅቡቲ ወደቦች እና ነፃ የንግድ ቀጣናዎች ባለሥልጣን እንዲሁም ለፕሮጀክቱ ድጋፍ ላደረጉ ሌሎች አካላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም