ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በቀጣናው ሰላም፣ መረጋጋት እና ኢኮኖሚያዊ ውህደት እንዲሳለጥ በቁርጠኝነት እየሰራች ነው-ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 14/2019 (ኢዜአ):-ኢትዮጵያ በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ውህደቶች እንዲሳለጡ በቁርጠኝነት እየሰራች መሆኑን የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ገለጹ። 

ፕሬዝዳንት ታዬ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት 81ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት በዓለም ደረጃ ፍትሃዊ ሥርዓት ማንበር ሁሉንም ተጠቃሚ ለማድረግ ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።

ዘላቂ ሠላም የሚረጋገጠው በሉዓላዊ እኩልነት ላይ በተመሰረተ ትብብር ብቻ ነው ያሉት ፕሬዝዳንት ታዬ፣ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በጸጥታ ጉዳዮች ላይ በጋራ መሥራት ወሳኝ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል። 

በጸጥታ ጉዳዮች ላይ በሚጠበቀው ደረጃ በጋራ አለመሰራቱ የኃይል ፖለቲካ እያየለ መምጣት ጋር ተዳምሮ የዓለም አቀፉን ሥርዓት ተጽዕኖ ውስጥ እየከተተው መሆኑን አስገንዝብዋል።

ለዚህ ችግር ሁነኛ መፍትሄ የባለብዙ ወገን ትብብር መሆኑን አንስተው ይህን ማድረግ ሲቻል ከግጭት ነጻ ዓለምን ማጽናት ያስችላል ሲሉ ተናግረዋል።     

ከ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን በላይ ሕዝብ የሚኖርባትን አፍሪካ ትርጉም ያለው ውክልና መከልከል አግባብነት የሌለው መሆኑንም አጽንዖት ሰጥተዋል።

ለዚህም በተለይም የጸጥታው ምክር ቤት ማሻሻያ እንዲደርግ ጥሪ አቅርበዋል።        

የሰው ሰራሽ አስተውሎት፣የአየር ንብረት ለውጥና በዓለም አቀፍ ደረጃ እየታየ ያለው የኢኮኖሚ አለመጣጣም ትልቅ ፈተና መደቀኑን ገልጸዋል።

በዚህ ረገድ የሚፈልቁ ቴክኖሎጂዎች በማደግ ላይ ያሉ ሀገራትን ጨምሮ ሁሉንም የዓለም ሕዝብን ተጠቃሚ ማድረጋቸውን ማረጋገጥ ወሳኝ ጉዳይ ነው ብለዋል።          

በምሥራቅ አፍሪካ ሠላምና ቀጣናዊ የልማት ትብብር እውን እንዲሆን ኢትዮጵያ በቁርጠኝነት እንደምትሰራ ያረጋገጡት ፕሬዝዳንት ታዬ፤ በሱዳን ለተከሰተው ግጭት በሱዳናውያን ባለቤትነት የሚመራ መፍትሄ እንዲበጅለትም ጥሪ አቅርበዋል።      

የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለቀጣናዊ ዕድገት አስተዋጽኦ የሚያበረክት ታላቅ የፓን-አፍሪካ የኃይል ፕሮጀክት መሆኑንም አብራርተዋል።      

የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያ ሽግግግር ለማስቀጠል አስተማማኝ የባህር በር ማግኘት ቁልፍ ጉዳይ ነው ያሉት ፕሬዝዳንት ታዬ፤ ኢትዮጵያ ከባህር በር ጋር የተያያዙ ዕድሎችን ለመጠቀም ሁሉንም ዲፕሎማሲያዊ አማራጮች እየተከተለች እንደሚገኝም አስረድተዋል።       

ኢትዮጵያ በምግብ ዋስትና፣ በታዳሽ የኃይል ምንጭ፣ በአረንጓዴ አሻራ እና አካባቢ ጥበቃ ሥራዎች ያስመዘገበቻቸውን አመርቂ ውጤቶችንም አንስተዋል።     

የዲጂታል ልማትን በማሳለጥ በኩል በርካታ ውጤታማ ተግባራት የተከናወኑ ሲሆን በ5 ሚሊዮን ኮደሮች ፕሮግራም የተመዘገበውን ስኬት በአብነት ጠቅሰዋል።

 

 

   

 

  

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም