የነዳጅ ማስተላለፊያ ቱቦው የሎጂስቲክስ ወጪና ጊዜን ትርጉም ባለው መልኩ ይቀንሳል- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የነዳጅ ማስተላለፊያ ቱቦው የሎጂስቲክስ ወጪና ጊዜን ትርጉም ባለው መልኩ ይቀንሳል- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ መስከረም 14/2019 (ኢዜአ):- በኢትዮጵያና ጅቡቲ መካከል የሚዘረጋው አዲስ የተጣራ ነዳጅ ማስተላለፊያ ቱቦ የሎጂስቲክስ ወጪና ጊዜን ትርጉም ባለው መልኩ የሚቀንስ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጅቡቲ ዳመርጆግ ከኢትዮጵያ ደወሌን የሚያገናኘውን የነዳጅ ምርቶች ማስተላለፊያ ቱቦ ግንባታ መሠረተ ድንጋይ የማስቀመጥ ሥነ-ሥርዓት ላይ ታድመዋል።
በጅቡቲ ዳመርጆግን ከኢትዮጵያ ደወሌ የሚያገናኝ እና ታላቅ ስትራቴጂካዊ ኢንቨስትመንት የሆነውን አዲስ የተጣራ ነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧ መስመር ዝርጋታ ዛሬ ይፋ ሆኗል።
መልክዓ ምድር ለሁለቱ ሀገራት የሰጠው የጋራ ኮሪደር ጅቡቲን ከሰፊ ገበያ፣ ኢትዮጵያን ደግሞ ወደ ዓለም አቀፍ ንግድ የሚያገናኝ ድልድይ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
የትራንስፖርት መዘግየቶች፣ ውስን የማጠራቀሚያ አቅሞች እና ውጤታማ ያልሆኑ የመጓጓዣ ዘዴዎች ለንግዱ ማህበረሰብ ከፍተኛ ወጪ ማስከተላቸውን አውስተዋል።
ዛሬ አዲስ አበባ የሚገባ እያንዳንዱ ሊትር ነዳጅ በመኪና አምስት ቀናትን አሳልፎ እንደሚመጣ ጠቅሰው አዲሱ የቧንቧ መስመር ይህንን ጉዞ ወደ አንድ ቀን ገደማ ዝቅ እንደሚያደርገው አመልክተዋል።
ጅቡቲ፣ ኢትዮጵያ እና የዳንጎቴ ግሩፕ በጋራ በመሆን ከዳመርጆግ እስከ ደወሌ 120 ኪሎ ሜትር የሚረዝም የነዳጅ ቧንቧ መስመር እንደሚዘረጉም ነው የጠቆሙት።
በሁለቱም ወገኖች ከአንድ ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር በላይ የሚሆን የጋራ ማከማቻ ቦታ የሚዘጋጅ ሲሆን፣ ይህም ዓለም አቀፍ ቀውሶች ሲያጋጥሙ የኢነርጂ አቅርቦቱ እንዳይስተጓጎል ዋስትና ይሰጣል ብለዋል።
መሠረተ ልማቱ ለኢትዮጵያ ኢንዱስትሪዎች እና ግብርና ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለጅቡቲ ደግሞ የትራንዚት መጠንን ከፍ በማድረግ እንደ ቀጠናዊ የሎጂስቲክስ ማዕከል ያላትን ቦታ እንደሚያጠናክር አብራርተዋል።
ወደቦች፣ አውራ ጎዳናዎች፣ የባቡር መስመሮች፣ ሞጆ የሎጂስቲክስ ማዕከል እና የቧንቧ መስመሩ እንደ አንድ የተሳሰረ ሥርዓት መሥራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
አሊኮ ዳንጎቴ፣ የአፍሪካ ድርጅቶች ከታላቅ ራዕይ ጋር የሚመጥን ግብ አሳክተው በዓለም አቀፍ ደረጃ መወዳደር እንደሚችሉ ማስመስከር መቻላቸውን ጠቅሰዋል።
ይህ ፕሮጀክት በአፍሪካዊ ካፒታል የተገነባ ለአፍሪካዊ ዕድገት የሚውል አፍሪካዊ መሠረተ ልማት ነው ብለዋል።
ሥራውን ወደ መሬት አውርዶ ውጤታማ ማድረግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዚህ ኢንቨስትመንት ፕሮጀክት እውን መሆን አስተዋፅኦ ላደረጉ አካላት ሁሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።