ቀጥታ፡

በምንከፍለው ግብር ከተማችን በልማት እያደገችና እየተለወጠች በመሆኑ ተደስተናል- የደሴ ከተማ ነጋዴዎች

ደሴ፤ መስከረም 14/2019(ኢዜአ)፡-በምንከፍለው ግብር ከተማችን በልማት እያደገችና እየተለወጠች በመሆኑ ተደስተናል ሲሉ የደሴ ከተማ ነጋዴዎች ገለፁ።

የደሴ ከተማ አስተዳደር በአዲሱ የፌዴራል ታክስ አስተዳደር ዙሪያ ከነጋዴዎች ጋር የግንዛቤ ማስጨበጫ የምክክር መድረክ አካሄዷል።

በወቅቱም ነጋዴዎቹ የሚከፍሉት ግብር የከተማዋን ልማት ለማሳለጥ በመዋሉ ከተማዋ እየተለወጠች ትገኛለች ብለዋል።

ከተሳታፊ ነጋዴዎች መካከል አቶ መሀመድ አሊ፤ የሚጠበቅባቸውን ግብር በወቅቱ በመክፈል የዜግነት ግዴታቸውን እየተወጡ መሆኑን ጠቁመው፣ "በምንከፍለው ግብር ከተማችን እያደገችና እየተለወጠች በመሆኑ ተደስተናል" ብለዋል። 

በዓመት በአማካይ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ግብር እንደሚከፍሉ የተናገሩት አቶ መሀመድ፣ ዘንድሮም የሚጠበቅባቸውን ግብር በወቅቱ በመክፈል በከተማዋ ልማት እየተሳተፉ መሆኑን ገልጸዋል።

ሌላው ተሳታፊ አቶ ጋሻው አሰፋ በበኩላቸው፤ "የአካባቢያችንን ሰላም ነቅተን በመጠበቅ ለከተማችን ሁለንተናዊ እድገትና ልማት የድርሻችንን እየተወጣን እንገኛለን" ሲሉ ገልጸዋል። 


 

"ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በከተማችን በተሰሩልን ልማቶች ተጠቃሚ መሆን ችለናል" ያሉት አቶ ጋሻው፣ የሚከፍሉትን ግብር ጠቀሜታ በተግባር ማየት በመቻላቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል። 

በሰሩት ልክ በየዓመቱ ከ100 ሺህ ብር በላይ ግብር በመክፈል ለሰላምና ልማት ስራው አስተዋጽኦ ማበርከታቸውንም አውስተዋል። 

በከተማዋ የተገነቡት የኮሪደር ልማትና ሌሎች የልማት ተግባራት የግብርን ፋይዳ እንዲገነዘቡ እንዳስቻላቸው ጠቁመው፣ የተጀመረውን ልማት ለማስቀጠል የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የደሴ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች መምሪያ ኃላፊ አቶ መንግስቱ አበበ በበኩላቸው፤ በከተማዋ የሚካሄደው ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ የሚያመነጨውን ገቢ አሟጦ በመሰብሰብ ልማትና ዕድገቷን ለማፋጠን እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። 

በአዲሱ የፌዴራል ታክስ አስተዳደር ዙሪያ ለንግዱ ማህበረሰብ ግንዛቤ በመፍጠር፣ አስተዳደሩ ያቀደውን ከ8 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ እየሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።


 

የደሴ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ሽመልስ ጌታቸው በበኩላቸው፤ ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን የከተማዋን ሰላም በመጠበቅ ሰፋፊ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን አብራርተዋል።

የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ፍቅረ ማሪያም ደጀኔ በበኩላቸው፤ በክልሉ በሚንቀሳቀሰው ኢኮኖሚ ልክ ገቢ በመሰብሰብ የልማት ሥራዎችን ለማከናወን የግብር ከፋዩ ህብረተሰብ ድርሻ የጎላ መሆኑን ገልጸዋል። 


 

በዚህም ባለፉት ዓመታት ውጤታማ ተግባር መከናወኑን ጠቁመው፣ ዘንድሮም የተሻለ ለመስራት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በምክክር መድረኩ የክልል፣ የከተማና የክፍለ ከተማ አመራሮችን ጨምሮ ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም