የመስቀል በዓል ሀይማኖታዊ ፣ታሪካዊና ባህላዊ እሴትን በጠበቀ መልኩ ይከበራል - ኢዜአ አማርኛ
የመስቀል በዓል ሀይማኖታዊ ፣ታሪካዊና ባህላዊ እሴትን በጠበቀ መልኩ ይከበራል
ጎንደር፤ መስከረም 14 /2019 (ኢዜአ)፡-የመስቀል በዓል ሃይማኖታዊ፣ታሪካዊና ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ የህዝብን አንድነትና ሰላም በሚያረጋግጥ መልኩ እንደሚከበር የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ገለፁ።
የመስቀል በዓል አከባበርን አስመልክቶ ከጎንደር ከተማ ወጣቶች ጋር የውይይት መድረክ ተካሒዷል።
የከተማዋ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ቻላቸው ዳኘው በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ የመስቀል በዓል የጎንደር ከተማ ታሪካዊና ባህላዊ እሴት፣ የህዝቦቿ አንድነትና የማንነት ማሳያ ነው።
የበዓሉ መከበር ከመላው ኢትዮጵያና ከውጭ ሀገራት የሚመጡ እንግዶችንና ጎብኚዎችን በመቀበል የከተማዋን መልካም ገጽታ ለማስተዋወቅ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም ተናግረዋል።
በዓሉ ይበልጥ አምሮና ደምቆ በሰላማዊ መንገድ እንዲከበር የከተማው ህዝብ፣ በተለይም ወጣቱ በባለቤትነት ስሜት እንዲሳተፍ አሳስበዋል።
የከተማው ሰላምና ጸጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ አለልኝ ዓለም በበኩላቸው፤ የመስቀል በዓል ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቱን ጠብቆ በሰላም እንዲከበር ወጣቶች የላቀ ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።
በመሆኑም ከዋዜማው ጀምሮ በሚካሔደው የደመራ በዓለልም ሆነ በመስቀል እለት ተቀጣጣይ ቁሶችን ይዞ መንቀሳቀስ በፍፁም የተከለከለ መሆኑን አሳስበዋል።
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ስልጣናት አባ ዮሴፍ ደስታ፤ በዓሉ ሲከበር ፍፁም ሃይማኖታዊና መንፈሳዊ እሴቱን በጠበቀ መልኩ ሊሆን እንደሚገባ ገልጸዋል።
መስቀል የፍቅርና የሠላም መገለጫ በመሆኑ ከሃይማኖት ውጭ የሆኑ የተሳሳቱ ተግባራት እንዳይታዩ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ነው ያሳሰቡት።
ክርስቶስ ጥልና ጥላቻን የገደለበት የተቀደሰ በዓል በመሆኑ በዓሉ በባህላዊ አልባሳት በመድመቅና መንፈሳዊ መዝሙሮችን በመዘመር እንደሚከበርም ነው የተናገሩት።
በዓሉ የሃይማኖታዊ ትውፊቱን ጠብቆ እንዲከበር ወጣቱ የበኩሉን ሚና ለመወጣት ተዘጋጅቷል ያለው ደግሞ ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል የሆነው ወጣት ሰለሞን አስፋው ነው።