የሕዳሴ ዋንጫ የጋራ ጥረት ስኬት እና ድል የሚዘክር ትእምርት ነው - አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር - ኢዜአ አማርኛ
የሕዳሴ ዋንጫ የጋራ ጥረት ስኬት እና ድል የሚዘክር ትእምርት ነው - አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር
አዲስ አበባ፤ መስከረም 14/2019 (ኢዜአ):-የሕዳሴ ዋንጫ የኢትዮጵያውያንን የጋራ ጥረት ስኬት እና ድል የሚዘክር ትእምርት ነው ሲሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሀገራዊ ቅርስነት በአድዋ ድል መታሰቢያ ውስጥ በክብር እንዲያርፍ የተወሰነለትን የሕዳሴ ዋንጫ ለአድዋ ድል መታሰቢያ አስረከቧል።
የሕዳሴ ዋንጫ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የሚውል ገቢ ለማሰባሰብ በመላ ኢትዮጵያ በመዘዋወር የኢትዮጵያን ሕዝቦች ያሳተፈ ታሪካዊ ተልዕኮ ማከናወኑ ይታወሳል።
ዋንጫው ኅዳር 29 ቀን 2018 ዓ.ም በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ሆሳእና ከተማ "ዴሞክራሲያዊ መግባባት ለኅብረብሔራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሃሳብ በተከበረው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ላይ ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ማስረከባቸውም እንዲሁ።
የፌዴሬሽን ምክር ቤትም በዛሬው እለት ይህን ታሪካዊ ዋንጫ ለአድዋ ድል መታሰቢያ አስረክቧል።
በመርሀ ግብሩ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገርን ጨምሮ፣ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር)፣ የአድዋ ድል መታሰቢያ ዋና ዳይሬክተር ዮሴፍ ቤኮ (ዶ/ር)፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አመራሮች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር በዚሁ ወቅት እንዳሉት የሕዳሴ ዋንጫ የኢትዮጵያውያንንን የጋራ ጥረት ስኬት እና ድል የሚዘክር ትእምርት ነው።
ይህ ዋንጫ ርክክቡ የላቀ ትርጉም እንዳለውም ነው አፈ ጉባኤው ጨምረው የተናገሩት።
የሕዳሴ ዋንጫ የቁርጠኝነት እና በመስዋእትነት የተጻፈ የህዝብ አሻራ መሆኑን ጠቁመው፤ በመላው ኢትዮጵያውያን የተጻፈ የድል ትእምርት መሆኑንም አክለዋል።
የሕዳሴ ዋንጫ የኢትዮጵያውያንን የጋራ ጥረት እና ስኬት የሚዘክር መሆኑንና መላው ኢትዮጵያውያንን ያቆራኘ አምባሳደር ነው ብለዋል።
የሕዳሴ ዋንጫ በራስ አቅም መስራት እንደሚቻል ያሳዩበት የመስዋእትነት አሻራ እንደሆነም ነው የገለጹት።
በአድዋ ድል መታሰቢያ እንዲቀመጥ የተደረገው የኢትዮጵያውያን የቁርጠኝነት ማሳያ የሆነው የሕዳሴን ግድብ ዋንጫ፣ የኢትዮጵያን የጋራ ጥረት ስኬት የሚዘክር ቅርስ እንደሆነም ተናግረዋል።
የነገ ሀገር ተረካቢ የሆኑ ትውልዶች ታላላቅ የጋራ ታሪክ ለመስራት መነሳሳትን እንደሚፈጥርም ገልጸዋል።
የአድዋ ድል መታሰቢያ ዋና ዳይሬክተር ዮሴፍ ቤኮ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የዛሬው የሕዳሴ ዋንጫ ርክክብ ከታሪካዊ ቦታ ጋር የተገናኘበት ነው ብለዋል።
የሕዳሴ ዋንጫ ለትውልዱ ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ መሆኑንም አክለዋል።