የኢትዮ-ጅቡቲ ወዳጅነት፡የመደመር መንግሥት የጎረቤት ተኮር ዲፕሎማሲ ህያው አብነት - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮ-ጅቡቲ ወዳጅነት፡የመደመር መንግሥት የጎረቤት ተኮር ዲፕሎማሲ ህያው አብነት
የኢትዮጵያና የጅቡቲ ሕዝቦች በታሪክ፣በቋንቋ፣ በባህልና በማኅበራዊ እሴቶች እጅግ የተሳሰሩና በደም የተቆራኙ ወንድማማቾች ናቸው።የሀገራቱ የትብብር ታሪክም ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ የተሻገረ ሆኖ ይገኛል።
ኢትዮጵያ በዳግማዊ አፄ ምኒሊክ ዘመነ መንግሥት የመጀመሪያውን ቆንስላ ጽሕፈት ቤት በጅቡቲ ከፍታለች።ለኢትዮጵያ በታሪኳ የመጀመሪያው የውጭ አገር ዲፕሎማሲያዊ ተልዕኮ ነበር።
እ.አ.አ በ1897 የፈረንሳይ አስተዳደር ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በመስማማት ጅቡቲን ከአዲስ አበባ የሚያገናኘውን ታሪካዊ የባቡር መስመር ግንባታ አስጀምሯል።
ይህ መሠረተ ልማት የሁለቱን አገራት የንግድና የሕዝብ ትስስር ከመነሻው ያጠናከረ ዋነኛ ምሰሶ ነው።
የኢትዮጵያና የጅቡቲ ሕዝቦች በታሪክ፣ በቋንቋ፣ በባህልና በማኅበራዊ እሴቶች እጅግ የተሳሰሩና በደም የተቆራኙ ወንድማማቾች ናቸው።
ይህ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር የፖለቲካና የኢኮኖሚ ግንኙነቱ ጠንካራ መሠረት ተደርጎ የሚወሰድ ሲሆን ባለፉት አስርት ዓመታት ውስጥ በሀገራቱ መካከል ግዙፍ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች መገንባታቸው ትስስሩን ስትራቴጂካዊ መልክ እንዲይዝ አስችሏል።
ይህንን ትስስር ይበልጥ ዘላቂ ለማድረግ ዘመናዊው የአዲስ አበባ-ጅቡቲ የኤሌክትሪክ ባቡር መስመር፣ የድንበር ማቋረጫ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች፣ የፍጥነት መንገዶች እና የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ተዘርግተዋል።
ይህም አገራቱን በፖለቲካዊ ስምምነት ብቻ ሳይሆን በመሠረተ ልማት አስተሳስሯቸዋል።
በአሁኑ ወቅት ደግሞ ትስስራቸው ይበልጥ እያደገ መጥቷል። በሁለቱ ሀገራት መሪዎች መካከል የሚደረጉ የጉብኝት ልውውጦችም ትስስሩን የማጠናከር ወሳኝ ሚና እየተወጣ ይገኛል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተለያዩ ጊዜያት ወደ ጅቡቲ በማቅናት እንዲሁም የጅቡቲው ፕሬዝዳንት እስማኤል ዑመር ጊሌ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት የሁለትዮሽና ቀጣናዊ ትስስሮችን የሚያጠናክሩ ውይይቶችን አድርገዋል።
ኢትዮጵያ ቅድሚያ ለጎረቤት በሚሰጠው የመደመር መንግሥት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋ አማካኝነት በቀጣናው በምታደርገው የልማት ትስስር የኢትዮ-ጅቡቲ ወዳጅነት በአብነት የሚነሳ ነው።
የኢትዮ-ጅቡቲ ወዳጅነት በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ የተመሠረተ ሲሆን፤ በሀገራቱ መካከል የተመሠረተው የሕዝብ ለሕዝብ መድረክ እንደ ፍልሰት እና የአየር ንብረት ለውጥ ያሉ የጋራ ተግዳሮቶችን በጋራ ለመፍታት ያስችላል።
የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ ተሞክሮን በጅቡቲ ጭምር የማጋራትና የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሮች ተግባራዊ ማሳያ ናቸው።
በዛሬው ዕለት ደግሞ ይህንን ጠንካራ ወዳጅነት ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር ስትራቴጂካዊ ትስስር ተበስሯል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ የጅቡቲ ፕሬዚዳንት እስማኤል ዑመር ጊሌ እና አፍሪካዊው ባለሀብት አሊኮ ዳንጎቴ በጋራ ዛሬ አዲሱን የትብብር ምዕራፍ አስጀምረዋል።
ይህም በጅቡቲ ዳመርጆግን ከኢትዮጵያ ደወሌ የሚያገናኝ አዲስ የተጣራ ነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧ መስመር ዝርጋታ ፕሮጀክት ነው።
ፕሮጀክቱ በሁለቱም ጫፎች የሚገነቡ የማከማቻ ተርሚናሎችን የሚያካትት ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስና በዳንጎቴ ግሩፕ ጥምረት የሚተገበር ነው።
ዋና ዓላማው የነዳጅ ማጓጓዣ ወጪንና መዘግየትን በመቀነስ፣ የኢነርጂ አቅርቦትን ማሻሻል እና የኢትዮ–ጅቡቲ የንግድ ኮሪደርን ይበልጥ ማቀላጠፍ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንደገለጹትም፣ ፕሮጀክቱ የሎጂስቲክስ ወጪንና መዘግየትን በመቀነስ የኢነርጂ ዋስትናን ያጠናክራል፤ የኢትዮ–ጅቡቲ የንግድ መስመርንም ፍጥነትና ዘላቂነት ያሳድጋል።
ነገር ግን ይህ መሠረተ ልማት ከነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧ መስመር በላይ የሚታይ ትርጉም አለው።
ከንግድና ከሎጂስቲክስ ባሻገር፣ በአፍሪካውያን ኢንቨስትመንትና በጋራ ልማት ላይ የተመሠረተ ቀጣናዊ ትስስርን የሚያጠናክር አዲስ የትብብር ደረጃ ነው።
ይህም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሚመራው የመደመር መንግሥት የሚከተለው የቅድሚያ ለጎረቤት የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ጅቡቲን ጨምሮ በቀጣናው የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያጎለብቱ አስተሳሳሪ ልማቶችን በመተግበር ቀጣናዊ ትስስርን ለማጠናከር የሚከተለውን አቅጣጫ ያሳያል።
የኢትዮጵያ እና የጅቡቲ የመጻኢ ጊዜ የሁለትዮሽ ትብብር በሀገራቱ መካከል የተጀመሩትን ግዙፍ የምጣኔ ሀብት እና የመሠረተ ልማት ትስስሮች ይበልጥ ወደ ላቀ የተሟላ ቀጣናዊ ትስስር የሚሸጋገርበት ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
የሁለቱ አገራት መሪዎች እና ሕዝቦች ያላቸው ዘመን ተሻጋሪ ወዳጅነት፣ የጋራ ህልውና እና እምነት የወደፊት ወዳጅነታቸውን ይበልጥ አስተማማኝ እንደሚያደርገው ይታመናል።