በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ለቱሪዝም መስክ የተሰጠው ትኩረት ለውጥ እያስመዘገበ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ለቱሪዝም መስክ የተሰጠው ትኩረት ለውጥ እያስመዘገበ ነው
አርባምንጭ ፤መስከረም 14/2018 (ኢዜአ)፡- በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ለቱሪዝም መስክ የተሰጠው ትኩረት ሰፊ መነቃቃትና ለውጥ እያስመዘገበ መሆኑን በአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ የዘርፉ ምሁራን ገለጹ።
በአገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሙ ትኩረት ከተሰጣቸው አምስቱ የኢኮኖሚ ምሰሶዎች መካከል የቱሪዝም ዘርፍ አንዱ ነው፡፡
ዘርፉ ለኢኮኖሚው እድገት ያለውን አቅም ለማሳደግም ተፈጥሯዊና ታሪካዊ መስህቦችን የማልማትና የማስተዋወቅ ስራ በስፋት እየተከናወነ ነው፡፡
በተለይም ባለፉት ጥቂት አመታት ነባር መዳረሻዎችን ከማሻሻል ባለፈ አዳዲስ መዳረሻዎችን የማልማት ስራዎች ተከናውነዋል፤ እየተከናወኑም ይገኛሉ።
በጉዳዩ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ የዘርፉ ምሁራን እንዳሉት መንግስት በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው የብዝሀ ዘርፍ ኢኮኖሚን በመተግባር የስራ እድልን ማስፋትና ዘላቂ እድገትን ማስመዝገብ ችሏል።
ይህም የሀገሪቱን ቱሪዝም መስክ መነቃቃት በመፍጠር የህብረተሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እያገዘ ነው።
በዩኒቨርሲቲው የሆቴልና ቱሪዝም አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ አሰግድ አየለ (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያን የቱሪዝም መስህቦች በተፈለገው መጠን ማልማት ባለመቻሉ ዘርፉ ተገቢውን ጥቅም ሳይሰጥ ቆይቷል።
ይህን አሰራር ለመቀየር በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተጀመሩት የገበታ ለሀገር እና ለትውልድ እንዲሁም የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማቶች የቱሪዝም ኢኮኖሚውን እንዲነቃቃ ማድረጉን ገልጸዋል።
የቱሪስት መሰረተ ልማቶች ግንባታና በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ሀይል ልማትም ቱሪዝም ኢኮኖሚን ከመገንባት ባለፈ የሀገር ገጽታንና የህዝቦችን ትስስር በማጠናከር ረገድ ጉልህ ፋይዳ ማበርከቱን ጠቅሰዋል።
የቱሪዝም ፀጋዎችን በማልማትና በማስተዋወቅ ረገድ ባለፉት ጥቂት አመታት የተከናወኑ ስራዎች አበረታች መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የቱሪዝምና ሆቴል አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ፌኔት ሚደቅሳ ናቸው።
በዚህም የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገራት ቱሪስቶችን ቆይታን በማራዘም የዘርፉን ኢኮኖሚ ልማት ማፋጠኑንና ፣ ለስራ ዕድል ፈጠራና ለውጭ ምንዛሬ ግኝት የላቀ ሚና ማበርከቱን ጠቁመዋል።
ለዘርፉ ዕድገት የአገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ለቱሪስቱ ምቹ ማድረግና የዲጅታል አገልግሎት በመጠቀም የማስተዋወቅ ስራዎችም መጠናከራችውን ጠቁመዋል።
የቱሪዝም ዘርፉ ለሀገር ዕድገት ያለውን አቅም ለማስፋት በሚደረገው ጥረት ምሁራኑ በጥናትና ምርምር እያገዙ መሆናቸውን ተናግረዋል።