የመስቀል ደመራና የኢሬቻ በዓላት ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶቻቸውን ጠብቀው በድምቀት እንዲከበሩ የተቀናጀ ዝግጅት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
የመስቀል ደመራና የኢሬቻ በዓላት ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶቻቸውን ጠብቀው በድምቀት እንዲከበሩ የተቀናጀ ዝግጅት ተደርጓል
አዲስ አበባ፤ መስከረም 14/2019 (ኢዜአ):-የ2019 ዓ.ም የመስቀል ደመራና የኢሬቻ በዓላት ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶቻቸውን ጠብቀው በድምቀት እንዲከበሩ የተቀናጀ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ገለፀ።
ቢሮው በዓላቱን በድምቀት እንዲከበሩ የተደረገ ቅድመ ዝግጅትን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።
የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ምክትል ቢሮ ሃላፊ ፍስሀ ጥበቡ በመግለጫቸው እንዳሉት፥ የዕድገትና የልማት ጉዞ ዘላቂ የሚሆነው አስተማማኝ ሰላምና ማህበራዊ መተሳሰብ ሲኖር ነው።
በዓላቱ ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶቻቸውን ጠብቀው በድምቀት እንዲከበሩ ከፀጥታ አካላት፣ ከሃይማኖትና ባህል ተቋማት እንዲሁም ከኅብረተሰቡ ጋር የተቀናጀ ሥራ መከናወኑን ጠቁመዋል።
የመስቀል ደመራ እና የኢሬቻ በዓላት ከሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶቻቸው ባሻገር፣ በማህበራዊ ትስስር፣ በሰላም ግንባታ እና በህዝቦች አብሮነት ላይ ባላቸው የጎላ አስተዋጽኦ በዩኔስኮ በማይዳሰስ የዓለም ቅርስነት የተመዘገቡ መሆናቸው አመልክተዋል።
በዚህም በዓላቱ በድምቀት መከበራቸው የባህል እሴቶችን ከማስቀጠል ባለፈ ለሀገራዊ እድገት፣ ለቱሪዝም፣ ለንግድና ለማህበራዊ ካፒታል መጠናከር አወንታዊ እድልን እንደሚፈጥር ገልፀዋል።
ስለሆነም በዓላቱ ሲከበሩ አብሮነትን፣ መቻቻልንና የመከባበር ባህልን በሚያጠናክር መልኩ ሊሆን ይገባል ነው ያሉት።
የፀጥታ መዋቅሩ የህዝብን ደህንነት ከመጠበቅ በተጨማሪ የትራፊክ ፍሰትን የማስተካከል፣ መጨናነቅን የመቆጣጠር እና ለአደጋ ጊዜ ምላሽ የመስጠት ዝግጅቱን ማጠናቀቁንም አስታውቀዋል።
ቢሮው ከሚመለከታቸው የፀጥታ አካላት፣ ከሃይማኖት ተቋማት፣ ከአባ ገዳዎች፣ ከአደስንቄዎች እንዲሁም ከህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በመተባበር ሰፊ የቅድመ ዝግጅት እና የንቅናቄ ስራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን አስታውቋል።
የፀጥታ መዋቅሩ የበዓላቱን ህዝባዊ ባህሪ፣ የህዝብ ብዛትና የሚጠበቁ እንቅስቃሴዎችን ታሳቢ ያደረገ ዝግጅት ማድረጉን ገልፀው፤ የከተማዋ ነዋሪዎችና የበዓላቱ ታዳሚዎች የፀጥታ አካላትን መመሪያዎች እንዲከተሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።
መገናኛ ብዙሃንም በበዓላቱ ወቅት ትክክለኛ፣ ሚዛናዊና የተረጋገጡ መረጃዎችን ለህዝቡ በማድረስ እንዲሁም የሰላምና የመቻቻል መልዕክቶችን በማስተጋባት ሙያዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
የከተማዋ ነዋሪዎችና የበዓላቱ ታዳሚዎች ከፀጥታ አካላት ጋር የተለመደ ቅንጅቱን በማሳደግ ህግና ስርዓትን በማክበር እንዲሁም አጠራጣሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ ፈጣን ጥቆማ በመስጠት ሰላማዊነታቸውን እንዲያግዙ ጥሪ ቀርቧል።
በመጨረሻም ህብረተሰቡ በበዓላቱ አከባበር ማንኛውንም አጠራጣሪ ሁኔታዎች ወይም የፀጥታ ስጋቶች ሲያጋጥሙ በነፃ የስልክ መስመር 8882 በመደወል እንዲያሳውቅ ቢሮው ጥሪ አስተላልፏል።