የኢትዮጵያ-ጅቡቲ የነዳጅ ምርቶች ማስተላለፊያ መስመር የኢትዮጵያና ጅቡቲ ስትራቴጂካዊና ድንበር ተሻጋሪ የመሠረተ ልማት ውጥን ማሳያ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ-ጅቡቲ የነዳጅ ምርቶች ማስተላለፊያ መስመር የኢትዮጵያና ጅቡቲ ስትራቴጂካዊና ድንበር ተሻጋሪ የመሠረተ ልማት ውጥን ማሳያ ነው
አዲስ አበባ፤ መስከረም 14/2019 (ኢዜአ):- የኢትዮጵያ-ጅቡቲ የነዳጅ ምርቶች ማስተላለፊያ መስመር የኢትዮጵያና ጅቡቲ ስትራቴጂካዊና ድንበር ተሻጋሪ የመሠረተ ልማት ውጥን ማሳያ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ገለጸ።
ዓላማውም የኢትዮጵያን የኃይል ዋስትና ማሻሻል፣ ቀጣናዊ የንግድ ትስስርን ማሳደግ፣ እንዲሁም የነዳጅ ምርቶችን ከጅቡቲ ወደ ኢትዮጵያ አስተማማኝ እና እምነት በሚጣልበት ቀልጣፋ በሆነ መንገድ ማጓጓዝን ማረጋገጥ መሆኑንም ጽሕፈት ቤቱ አስታውቋል።
ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ እና በዳንጎቴ ግሩፕ መካከል በሚደረግ የጋራ ኢንቨስትመንት የሚከናወን መሆኑንምገልጿል።
ከጅቡቲዋ ዳመርጆግ እስከ ኢትዮጵያዋ ደወሌ ባለው መስመር ላይ ወደ 120 ኪሎ ሜትር ያህል የሚዘልቀው ይህ ፕሮጀክት፤ በዳመርጆግ የሚገኙትን የባሕር ላይ ነዳጅ መቀበያና የባሕር ዳርቻ ማከማቻ ተቋማትን በደወሌ ከሚገኙት የሀገር ውስጥ ማከማቻና ማከፋፈያ ተቋማት ጋር የሚያገናኝ የተቀናጀ የነዳጅ ሎጅስቲክስ ሥርዓት እንደሚዘረጋለትም አመላክቷል።
በዳመርጆግ ተርሚናል ላይ የተጣሩ የነዳጅ ምርቶች ወደ ተዘጋጁ ልዩ ማከማቻዎች የሚዘዋወሩ ሲሆን፤ ይህን ተከትሎ በኢትዮጵያ በስፋት እንዲሰራጩ ዘርፈ ብዙ አገልግሎት በሚሰጥ የነዳጅ ቱቦ አማካኝነት ወደ ደወሌ እንደሚጓጓዝም የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ገልጿል።