ቀጥታ፡

የባሌ ተራሮች እውነታ

በኢትዮጵያ ከሚገኙ ውብ እና አስደናቂ የተፈጥሮ መስህቦች መካከል የባሌ አካባቢ ልዩ ስፍራ የሚሰጠው ነው። የባሌ የተፈጥሮ ሀብት ከማራኪ መልክዓ ምድር ባለፈ የብርቅዬ እንስሳትና አእዋፋት መገኛም መሆኑ ይታወቃል። ከሰማይ ጠቀስ ተራሮቹ እስከ ጥቁር አንበሳ መኖሪያው የሃረና ደን፣ ከገዳ ስርዓት የጥበቃ እሴት እስከ ካርቦን ንግድ ተጠቃሚነቱ ባሌ በተፈጥሮ የታደለ እውነተኛ ድንቅ ምድር ነው፤ በአንድ አባባል፡ 'ባሌ፡ አንድ ፓርክ፣ የብዙ ዓለማት መገኛ! (Bale: One Park Many Worlds) እየተባለ የሚጠራው።

የባሌ መልክዓ-ምድር የተፈጥሮ ድንቅ ጥበብ ማሳያ ነው፤ የበርካታ ወንዞች ምንጭ፣ የጥቅጥቅ ደኖችና የአረንጓዴ ምድር ነፃብራቅ። ከባህር ጠለል በላይ ሰማይን በሚነኩ ግዙፍ ተራሮቹ፣ ሰፋፊ አምባዎቹና ውብ ሸለቆቹ የታጀበው ይህ አስደናቂ ስፍራ፣ በተፈጥሮ ለጋስነት ከተጎናፀፋቸው እምቅ የውሃ ሀብቶች ጋር ተደምሮ እውነተኛ የምድር ላይ ገነት ያደርገዋል።


 

የባሌ ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ ከ2 ሺህ 150 ካሬ ኪሎ ሜትር በላይ ስፋት ያለው ሲሆን በከፍተኛ ቦታዎች ላይ የተለያዩ የዕፅዋት ዝርያዎችን የያዘ እምቅ የደን ሀብትም አለው። መልክዓ ምድራዊ አቀማመጡም ሲታይ ከባህር ጠለል በላይ ዝቅተኛው 1 ሺህ 500 ሜትር እንዲሁም ከፍተኛው ጫፍ የቱሉ ዲምቱ ተራራ በ4 ሺህ 377 ሜትር ከፍታ ላይ የሚገኝ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ። በፓርኩ ከ260 በላይ የአእዋፍ ዝርያዎች እና ልዩ ልዩ ብርቅዬ የዱር አንስሳት የሚገኙ መሆኑም ይታወቃል። በዚህም ድንቅ ተፈጥሯዊና ብዝሃ-ሕይወታዊ ሀብቱ ምክንያት፣ የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በዩኔስኮ የዓለም የተፈጥሮ ቅርስ ሆኖ በቋሚነት መመዝገቡ ይታወቃል።

በባሌ ተጠቃሽ ከሆኑት የቱሪስት መዳረሻዎች መካከል ከ4 ሺህ ሜትር በላይ ከፍታ ላይ የሚገኘው በረዷማው የሳነቴ አምባ ይጠቀሳል። በዚህ አስደናቂ የተፈጥሮ እይታ ባለው አካባቢ ብርቅዬ የሆኑ ቀይ ቀበሮዎችን በቀላሉ ማየት ይቻላል።


 

የሃረና ጥቅጥቅ ደን ደግሞ ከሳነቴ አምባ በስተደቡብ በኩል የሚወርድ ሰፊና እርጥበታማ አካባቢ ሲሆን በዛፎች የተሞላ፣ በርካታ የዱር እንስሳት የሚገኙበት እንዲሁም ኩልል ያሉ አስደናቂ ፏፏቴዎች የሚገኙበት ነው። የሀገራችን ጋሻና መከታ የሆነው የጀግናው መከላከያ ሰራዊታችን ተምሳሌት የሆነው ብርቅዬው ጥቁር አንበሳ፣ በዚህ አስደናቂ የሃረና ተፈጥሮ ደን ውስጥ ይገኛል። የአካባቢው ማህበረሰብ ከገዳ ስርዓት በወረሰው ድንቅ ባህላዊ እሴትና ተፈጥሮን የመንከባከብ እውቀቱ ደኑን ጠብቆ በማቆየቱ፣ ከስነ-ምህዳሩ ከሚያገኘው በርካታ አገልግሎት ባሻገር፣ ዛሬ ላይ በአሳታፊ የደን አስተዳደር አማካኝነት ከካርቦን ሽያጭ ቀጥተኛ ተጠቃሚ መሆን ችሏል።


 

ለተራራ ላይ የእግር ጉዞ አፍቃሪ ጎብኚዎች ደግሞ የቱሉ ዲምቱ ተራራ ከነ ግርማ ሞገሱ የሚጠብቃቸው ይሆናል። ብርቅዬው ቀይ ቀበሮ ዋነኛ ምግቡ የሆነውን ፍልፈል የዓይጥ ዝርያ በቀስታ ሲያድንና ዘሎ በሹል አፉ ሲይዝ ማየት ለናፈቀው ጎብኚም ሳነቴ ተመራጩ ቦታ ነው። ባለ ክራቫቱ የደጋ አጋዘን ከእነግርማሞገሱ ቆሞ ፊትለፊት የሚታየው ደግሞ የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ አካል በሆነው ዲንሾ ጫካ ውስጥ ነው። 

የባሌ እና አካባቢው መልክዓ ምድር በአብዛኛው የሁለት ጊዜ የዝናብ ወቅት በመሆኑ ይህም ለምለምና አረንጓዴ እንዲሆን አድርጎታል። ከጎኑ እየታረሰ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የደረሰ ሰብል የሚሰበሰብበት ባሌ ለስንዴና ለቢራ ገብስ ልማት እጅግ ተመራጭና ተስማሚ የአየር ጠባይ እንዲሁም የመልክዓ-ምድር አቀማመጥ ያለው ምድር ነው። የእነዚህ ሁሉ ድምር ውጤቶች ባሌን እና የባሌ ተራሮች ብሄራዊ ፓርክን ተመራጭና ተወዳጅ የቱሪስት መዳረሻ ያደርገዋል።

በቅርብ ዓመታት እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች ባሌ ያለውን የተፈጥሮና የቱሪዝም አቅም ወደ ተጨባጭ የኢኮኖሚ ጥቅም ለመለወጥ እያስቻለ ይገኛል። ወደ ቱሪስት መዳረሻዎች የሚወስዱ የመንገድ ግንባታዎች፣ የኤሌክትሪክ እና የቴሌኮም መሰረተ ልማት ዝርጋታዎች በስፋት በመከናወን ላይ ይገኛሉ።

ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በመቀናጀት የሎጅ ግንባታዎች፣ የዕደ-ጥበብ ስራዎች ማስተዋወቅ እና እንግድነትን መሰረት ያደረጉ የኢኮ-ቱሪዝም ስራዎች ደረጃቸውን ጠብቀው እየተሰሩ መሆኑ ይታወቃል።

እንደ አጠቃላይ የባሌ የተፈጥሮ ሀብት፣ አስደናቂ መልክዓ ምድር፣ ብርቅዬ እንስሳትና አእዋፋት እንዲሁም የውሃ ሃብት ተደምሮ ለኢትዮጵያ ትልቅ የቱሪዝም ሃብት መሆን የሚችል ነው።

ከባሌ ሰፊ የተፈጥሮ ጸጋ ባለፈ በታሪክ፣ በባህል እሴቶችና በጠንካራ ማህበራዊ ትስስርም የሚጠቀስ ሲሆን የአካባቢው ማህበረሰብ ተፈጥሮን በማስጠበቅና በመንከባከብ ረገድ የዳበረ ልምድ እንዳለው ይታወቃል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም