ቀጥታ፡

ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ የሚገኘው የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር

አዲስ አበባ፤ መስከረም 14/2019 (ኢዜአ):- በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የተተገበረው የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ውጤቶች መገኘታቸውን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለጸ። 

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የግብርና ቢሮ ኃላፊ ማስረሻ በላቸው ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፤ በክልሉ ተግባራዊ የተደረገው የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የሚያስችል መሰረት ጥሏል።       

አርሶ እና አርብቶ አደሩ በመርሀ ግብሩ በስፋት እንዲሳተፍ በማድረግ በኩል ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውንም ጨምረው ገልጸዋል።

በዚህም አርሶ አደሩ የራሱን የምግብ ፍጆታ ከመሸፈን ባለፈ ምርቶችን ለገበያ በማቅረብ ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸው ውጤቶች ተመዝግበዋል ብለዋል።     

የወተት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በተደረገ ጥረት የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያዎች ላይ በተሰራ ስራ፤ በዓመት 69 ሺህ እንስሳትን በሰው ሰራሽና በተፈጥሯዊ መንገድ የማዳቀል አቅም መፈጠሩን ተናግረዋል።     

በዚህም በክልሉ በዓመት 390 ሚሊየን ሊትር ወተት የማምረት አቅም መፈጠሩን አቶ ማስረሻ ገልጸዋል።       

ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የቦንጋ ዶሮ እርባታ ማዕከል አቅም እንዲያደግ የተደረገ ሲሆን ማዕከሉ ከ15 እስከ 30 ሺህ ጫጩቶችን መፈልፈል የሚችል ማስፈልፈያ መሰረተ ልማት እንደተሟላለትም አስታውቀዋል።    

የአንድ ቀን የጫጩት አቅርቦት መጠን ማሳደግን በተመለከተም ወደ 2 ነጥብ 1 ሚሊየን ማሳደግ መቻሉን ጠቁመው፤ በዓመት ከ360 ሚሊየን በላይ እንቁላል ማምረት መቻሉ ስኬቶችን አመላካች መሆኑን ገልጸዋል።          

ከእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያ ማሽን ተከላ ጋር በተያያዘ እንደገለጹት በክልሉ 6 የመኖ ማቀነባበሪያ መሳሪያዎች ተተክለው ስራ ላይ ይገኛሉ።  

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አክለው እንደተናገሩት፤ የማር ምርት አቅርቦትን ለማሳደግ በተሰሩ ሥራዎች ክልሉ በአሁኑ ወቅት በዓመት 71 ሺህ ቶን ማር የማምረት አቅም ላይ ደርሷል።  

በክልሉ አርሶ እና አርብቶ አደሩ ዓሣን በጓሮው እንዲያመርት የማርቢያ መሰረተ ልማቶችን ጨምሮ የዓሣ ጫጩቶችን ተደራሽ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል። 

ለአብነትም 1ሺህ 600 ኩሬዎች መዘጋጀታቸውን ጠቁመው በዚህም አርሶ እና አርብቶ አደሩ ዓሣን በማምረት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱን እንዲያሳድግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። 

በክልሉ የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር የምግብ ዋስትና አቅርቦትን ከማሻሻል ባለፈ በሥራ ዕድል ፈጠራ በኩልም ከፍተኛ ውጤት እየተመዘገበበት እንደሚገኝም አቶ ማስረሻ በላቸው አብራርተዋል። 

 

 

 

  

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም