ከባህር በር ጥያቄ እስከ ፍትሃዊ ውክልና በተመድ ጉባኤ የተንጸባረቁ የኢትዮጵያ አቋሞች - ኢዜአ አማርኛ
ከባህር በር ጥያቄ እስከ ፍትሃዊ ውክልና በተመድ ጉባኤ የተንጸባረቁ የኢትዮጵያ አቋሞች
በኒውዮርክ እየተካሄደ የሚገኘው 81ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ የዓለምን ትኩረት የሳበና በርካታ አንገብጋቢ ጉዳዮች እየተነሱበት ይገኛል።
“መተማመንን ዳግም መገንባት እና አዳዲስ ለውጦችን በአግባቡ መምራት፣ ለሁሉም የሚሰራ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን መፍጠር” የጠቅላላ ጉባኤው መሪ ሀሳብ ነው።
በዚህ ዓለም አቀፍ መድረክ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ከፍተኛ ልዑካን ቡድን መሪ እና የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ያደረጉት ንግግር የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ አቋም፣ የልማት ጉዞ እና አህጉራዊ ራዕይ በሰፊው ያንጸባረቀ ነበር።
የፕሬዝዳንቱ መልዕክት የኢትዮጵያን ፍላጎቶች ከዓለም አቀፉ ነባራዊ ሁኔታ ጋር ያጣጣመና የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ አቅጣጫ ግልጽ ያደረገም ጭምር ነው።
ኢትዮጵያ 32ኛውን የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ-32) በታላቅ ዝግጅት እንደምታስተናግድ አብስረዋል።
ይህ ጉባኤ ከንግድ ተቋማት እስከ ዓለም አቀፍ ባለድርሻ አካላት ድረስ ሁሉን አካታች እና ተጨባጭ መፍትሄዎችን የሚያመጣ እንዲሆን ኢትዮጵያ በቁርጠኝነት እንደምትሰራ አረጋግጠዋል።
የአየር ንብረት ቀውሱን ለመከላከል ዓለም አቀፍ መሪዎች በኮፕ-32 ጉባኤ ላይ እንዲገኙ ጥሪ ያቀረቡት ፕሬዝዳንቱ፣ ሁሉም አካላት ታሪካዊ አሻራቸውን እንዲያሳርፉ አሳስበዋል።
መልዕክታቸውም በኢትዮጵያ በ8 ዓመታት ውስጥ የተተከሉት 56 ቢሊዮን ችግኞች፣ ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ጥበቃ ላይ ንግግር ብቻ ሳይሆን በቢሊዮን የሚቆጠሩ ዛፎችን በመትከል ከፍተኛ የካርቦን የመምጠጥ አቅም የፈጠረች ሀገር መሆኗን በሚገባ ያሳየ ነው።
የአየር ንብረት ርዕሰ ጉዳይን ተከትሎ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ እድገትና የባህር በር ጥያቄን በማንሳት ጠንካራ ሀሳቦችን አቅርበዋል። ጠንካራና የጸና ኢኮኖሚ ለመገንባት አስተማማኝ እና ደህንነቱ የተጠበቀ የባህር በር ማግኘት ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ የባህር በር ፍላጎት ከማንኛውም ሌላ ወገን ጥቅም ጋር የማይጋጭና ለቀጣናው ሀገራት የጋራ
ፕሬዝዳንቱ የባህር በር ማግኘት የሌሎችን ጥቅም እንደማይጎዳና ሁሉንም ወገኖች ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ማብራራታቸው፣ ጥያቄው በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ህጋዊና ሰላማዊ የልማት ጥያቄ ሆኖ እንዲወሰድ ትልቅ እድል የሚፈጥር ነው።
ዕድገትና ትብብር ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክት መሆኑን በግልጽ አስምረውበታል።
ይህንን ፍላጎት እውን ለማድረግም ሀገሪቱ ያላትን የዲፕሎማሲ አማራጮች በሙሉ በመጠቀም ከዓለም አቀፍ የንግድ ሥርዓት ጋር ለመተሳሰር እየሰራች መሆኑንም ገልጸዋል።
ይህም ኢትዮጵያ የባህር በር ማግኘት የሌሎችን ጥቅም እንደማይጎዳና ሁሉንም ወገኖች ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ማብራራታቸው፣ ጥያቄው በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ህጋዊና ሰላማዊ የልማት ጥያቄ ሆኖ እንዲወሰድ መንገድ ይከፍታል።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት አወቃቀር ላይ ሀሳባቸውን የሰነዘሩት ፕሬዝዳንት ታዬ፣ አንድ ነጥብ ስድስት ቢሊዮን የሚሆኑ አፍሪካውያን ተገቢውን ፍትሃዊ ውክልና ማጣታቸው በአስቸኳይ ሊታረም የሚገባው የሞራል ጥያቄ መሆኑን ተናግረዋል።
ተመድ የዓለምን ነባራዊ እውነታዎች ባገናዘበ መልኩ መሠረታዊ ሪፎርም ሊያደርግ እንደሚገባው አጥብቀው ያሳሰቡ ሲሆን፣ የአፍሪካን አህጉር በዓለም አቀፍ ውሳኔ ሰጪነት ውስጥ ማካተት የዘመኑ ግዴታ መሆኑን አብራርተዋል።
እውነተኛ የፖለቲካ ፍላጎት ካለ የአፍሪካ ህዝቦች የረጅም ጊዜ የውክልና መነፈግ አግባብነት እንደሌለው ጠቁመው፣ ይህ ጉዳይ የትውልዱ ትልቁ የህሊና እና የሞራል ጥያቄ መሆኑን አመልክተዋል።
የፕሬዝዳንቱ መልዕክት የአህጉሪቱን የጋራ አቋም የሚያጠናክር እና ኢትዮጵያ የቀደመች የተመድ መስራች አባልነቷን በመጠቀም የአፍሪካን ድምፅ በዓለም አቀፍ ደረጃ በግንባር ቀደምነት ተሞጋች ሆና እንድትቆም ያደርጋታል።
ከምግብ ዋስትና አንፃር ኢትዮጵያ ያስመዘገበችው ስኬት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በአጭር ጊዜ ውስጥ ከስንዴ አስመጪነት ወጥታ በአፍሪካ ግንባር ቀደም የስንዴ አምራች ሀገር መሆን የቻለችው ኢትዮጵያ፣ አፍሪካ በራሷ አቅም ራሷን መመገብ እንደምትችል በተግባር ማሳየቷን ተናግረዋል።
በተጨማሪም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በውሃ ሀብት አጠቃቀም ዙሪያ የጋራ ቀጣናዊ ብልጽግናን ማረጋገጥ እንደሚቻል ያረጋገጠ ታላቅ ፓን-አፍሪካዊ ፕሮጀክት መሆኑን አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ከ60 ሺህ ሜጋዋት በላይ የኃይል ማመንጨት አቅም እንዳላት ጠቅሰው፣ በቅርብ ዓመታት ውስጥ ተጨማሪ ኃይል በማመንጨት የምስራቅ አፍሪካን የኢነርጂ ፍላጎት ለማሟላት እቅድ ይዛ እየተንቀሳቀሰች መሆኑን አብራርተዋል።
ግድቡ የምስራቅ አፍሪካ የጋራ ብልጽግና እና የታዳሽ ኃይል ምንጭ ተደርጎ መቅረቡ የሀገሪቱን የልማት አተያይ ላይ መግባባት ለመፍጠርና የኢትዮጵያን ቀጣናዊ ተጽዕኖና ኢኮኖሚያዊ ትስስር የሚያጎላ ነው።
በቴክኖሎጂ እና በዲጂታል አብዮት ዘመን አፍሪካውያን ተመልካች ብቻ ሳይሆን የለውጡ ባለቤት መሆን እንደሚገባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል። የኢትዮጵያ የአምስት ሚሊዮን ኮደሮች መርሃ-ግብር እና የሰው ሰራሽ አስተውሎት ዩኒቨርሲቲ ግንባታ አህጉሪቱ ለዲጂታል ዘመን ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳዩ መሆናቸውን አስገንዝበዋል።
በአካባቢ ጥበቃ ረገድም ባለፉት ዓመታት የተከናወነው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርም ከሀገር አልፎ ዓለም አቀፍ ትኩረት የሰበሰበ ስኬት መሆኑን አብራርተዋል።
በስምንት ዓመታት ውስጥ 56 ቢሊዮን ችግኞች መተከላቸው የደን ሽፋንን ከማሳደግም በላይ ከፍተኛ መጠን ያለው ካርቦን የመምጠጥ አቅም በመፍጠር የዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ቀውስን ለመታገዝ የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።
ኢትዮጵያ ሰብአዊ ክብርን በሚያስከብር፣ ፍትሕ በሚያሰፍን እና በነጻ ህዝቦች ጽኑ አብሮነት ላይ በተመሰረተ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋ ጸንታ እንደምትቀጥል ፕሬዝዳንቱ አረጋግጠዋል።
በአጠቃላይ፣ የፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ንግግር ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ መድረክ መፍትሔ አመንጪ፣ የቀጣናው የኢኮኖሚ ትስስር መሪ እና የአፍሪካ ፍትሃዊ ውክልና ተሞጋች መሆኗን ያረጋገጠ መልዕክት ነው።