በኢትዮጵያ እና ጅቡቲ መካከል ታላቅ ስትራቴጂካዊ ኢንቨስትመንት የሆነ አዲስ የተጣራ ነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧ መስመር ዝርጋታ ይፋ ሆነ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ እና ጅቡቲ መካከል ታላቅ ስትራቴጂካዊ ኢንቨስትመንት የሆነ አዲስ የተጣራ ነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧ መስመር ዝርጋታ ይፋ ሆነ
አዲስ አበባ ፤ መስከረም 14/2019 (ኢዜአ):-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከፕሬዝዳንት ኢስማኤል ኦመር ጊሌ እና ከአሊኮ ዳንጎቴ ጋር በመሆን፣ በጅቡቲ ዳመርጆግን ከኢትዮጵያ ደወሌ የሚያገናኝ እና ታላቅ ስትራቴጂካዊ ኢንቨስትመንት የሆነውን አዲስ የተጣራ ነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧ መስመር ዝርጋታን ዛሬ ይፋ አድርገዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ ፕሮጀክቱ በሁለቱም ጫፎች ላይ በሚገነቡ የማከማቻ ተርሚናሎች የተደገፈ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ይህ ታሪካዊ መሰረተ ልማት በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ እና በዳንጎቴ ግሩፕ ጥምረት የሚተገበር ነውም ብለዋል።
የሎጂስቲክስ ወጭንና መዘግየትን በመቀነስ፣ የኢነርጂ ዋስትናን ያጠናክራል፤ እንዲሁም የኢትዮጵያ-ጅቡቲ የንግድ መስመርን ፍጥነት እና ዘላቂነትን ያሳድጋል ሲሉም ገልጸዋል።
መሰረተልማቱ ከነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧ መስመር ዝርጋታ በላይ፣ የአፍሪካውያንን ኢንቨስትመንት እና በጋራ መልማትን ማዕከል ያደረገ፣ ለዘላቂ እድገት፣ ለቀጣናዊ ትስስር እና ይበልጥ አስተማማኝ ለሆነ የጋራ ኢኮኖሚያዊ እጣ ፈንታ የሚደረግ ሰፊ ኢንቨስትመንት መሆኑንም አስታውቀዋል።