የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግርን እያረጋገጠ የሚገኘው አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ - ኢዜአ አማርኛ
የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግርን እያረጋገጠ የሚገኘው አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ
የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ለሀገር የኢኮኖሚ እድገት፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ እና ለውጭ ምንዛሬ ግኝት ዋና ማዕከል ነው። በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ታሪክ ውስጥ ዘርፉ የፖሊሲ እና መዋቅራዊ ፈተናዎች ሲያጋጥሙት የቆየ ቢሆንም፣ በየጊዜው በተወሰዱ የማሻሻያ እርምጃዎች፣ በኢንዱስትሪ ፓርኮች መስፋፋት እና በቅርብ ጊዜ በተጀመረው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም አማካኝነት ወደ አዲስ የስኬት እና የእድገት ምዕራፍ እየተሸጋገረ ይገኛል።
👉በኢንዱስትሪ ዘርፉ የነበሩ ፈተናዎች
በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ዘርፉ ተገቢው እድገት እንዳይመዘገብ በርካታ መዋቅራዊ ችግሮች ነበሩበት። የአምራች ኢንዱስትሪዎች የጥሬ፣ የካፒታል ዕቃዎች እና የፋብሪካ ማሽኖች እንዲሁም የማሽኖች መለዋወጫዎች ግዢ በውጭ ምንዛሬ ላይ የተመሰረቱ ናቸው። የውጭ ምንዛሬ እጥረት ደግሞ የማምረቻ ዘርፉ ብቻ ሳይሆን ሀገሪቷ ትልቁ ፈተና እንደነበር ይታወቃል። ይህ የውጭ ምንዛሬ እጥረት በአምራች ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም ላይ ከፍተኛ ችግር ሆኖ ቆይቷል።
ለኢንዱስትሪዎች ግብዓት የሚሆኑ የግብርና ምርቶች በሚፈለገው ጥራት እና መጠን አለመመረትም እንዲሁ አንዱ ተግዳሮት ሆኖ ይጠቀሳል። የግብርናው ዘርፍ ከኢንዱስትሪዎች ጋር ያለው የአቅርቦት ሰንሰለት በደላላ የተተበተበ፣ አምራቹንና ተቀባይ ኢንዱስትሪዎችን በቀጥታ ለማገናኘት እንቅፋት ሆኖ የቆየ ነበር።
ከአቅርቦት ሰንሰለቱ መበታተን በተጨማሪ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ፣ የመንገድ እና የሎጂስቲክስ ቀልጣፋ አለመሆን የምርታማነት ወጪን ከፍ አድርጎት መቆየቱም ይነሳል። አዳዲስ የኢንዱስትሪ ባለሀብቶች እና ነባር ፋብሪካዎች ለማስፋፊያ የሚሆን የረጅም ጊዜ ብድር የማግኘት እድላቸው ጠባብ ሆኖ መቆየቱም እንዲሁ ፋብሪካዎች ሙሉ አቅማቸውን እንዳይጠቀሙ አድርጓል።
👉ከችግር ወደ መፍትሔ መዋቅራዊ ሽግግር እና የፖሊሲ ማሻሻያዎች
ባለፉት ዓመታት በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሙ በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ይታዩ የነበሩ ስር የሰደዱ መዋቅራዊ ችግሮችን ለማቃለል እና የዘርፉን የኢኮኖሚ ዋና አንቀሳቃሽነት ሚና ለማሳደግ የመደመር መንግስት በርካታ የፖሊሲ እና የተግባር እርምጃዎችን ወስዷል።
አጠቃላይ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ የማምረት አቅም ከነበረበት 47 በመቶ ወደ 67 በመቶ ከፍ እንዲል ሰፊ ጥናቶችና የድጋፍ ስራዎች መከናወናቸውንና የወጪ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት የመተካት ስትራቴጂ ተግባራዊ መደረጉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 30ኛው መደበኛ ስብሰባ ላይ መግለጻቸው ዘርፉን ለማሳደግ መንግስት የወሰዳቸውን እርምጃዎች የሚያመላክት ነው።
መንግስት ከነባሮቹ የኮምቦልቻ፣ የመቀሌ እና የሐዋሳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች በተጨማሪ አስር አዳዲስ የኢኮኖሚ ዞኖችን በመገንባት ከ80 በመቶ በላይ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን መሳብ መቻሉን መጥቀሳቸውም ይህንኑ ያስረግጣል።
የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ምርቶች ዓለምአቀፍ ተወዳዳሪነትን የማሳደግና ለውጭ ገበያ የማቅረብ አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ ማደጉን እንዲሁም የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ በሀገሪቷ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ላይ የላቀ ሚና እያበረከተ መምጣቱን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል መግለጻቸው እንዲሁ የዘርፉን ውጤታማነት ያረጋግጣል።
በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ምክንያት በተነደፈው በ”ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ ዘርፉን ከመቼውም ጊዜ በላይ በማነቃቃቱ ለወጪ ንግድ የሚሆኑ ምርቶችን በመጠንም ሆነ በጥራት በማሳደግ የውጭ መንዛሬ ግኝት ላይ ትርጉም ያለው እድገት ተመዝግቧል። በተጨማሪም ኢትዮጵያ ከውጭ የምታስገባቸውን የተለያዩ ምርቶች በሀገር ውስጥ በማምረት ወደ ሀገር ይገቡ ለነበሩ ምርቶች ይወጣ የነበረውን የውጭ ምንዛሬ ማዳን የተቻለበት አቅምም ተፈጥሯል።
ኢትዮጵያ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን መሳብ የሚያስችሉ መሰረተ ልማቶችን ከማሟላት በተጨማሪ የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ስርዓትን በመዘርጋት የሀገር ውስጥ እና የውጭ ባለሀብቶችን በኢትዮጵያ ኢንቨስት የማድረግ ተነሳሽነት ማሳደግና ውጤት ማስመዝገብ አስችሏታል።
በተለይ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በተገነቡ የኢንደስትሪ ፓርኮች በተፈጠሩ የኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታዎችና በተሟሉ መሰረተ ልማቶች ተጠቅመው ምርቶቻቸውን ለውጭ ገበያ እያቀረቡ የሚገኙ አምራቾች ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደጉ መምጣታቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
እነዚህ የኢንዱስትሪ ፓርኮች የውጭ ኢንቨስትመንትን በመሳብ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር በማምጣትና ለዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር በኩል ትልቅ ሚና እየተጫወቱም ይገኛሉ። ፓርኮቹ የተቀናጀ መሰረተ ልማት እና ደረጃቸውን የጠበቁ አሰራሮች በማቅረብ ባለሀብቶች በፋብሪካ ግንባታ ላይ የሚያባክኑትን ጊዜ ቀንሰዋል።
👉የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ትሩፋቶች
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በኢትዮጵያ የማኑፋክቸሪንግ እና የኢንዱስትሪ ዘርፍ ላይ የተደቀኑ ችግሮችን ለመፍታት፣ የሀገር ውስጥ ምርታማነትን ለማሳደግና ኢንዱስትሪውን የኢኮኖሚው ዋና አንቀሳቃሽ ለማድረግ የተጀመረ ሀገራዊ ንቅናቄ ሲሆን አጠቀላይ በዘርፉ ያሉ ተግዳሮችን በመቅረፍ በኩል ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክቷል።
በዚህም ኢንደስትሪዎች ሲገጥማቸው የነበሩ የመሬት፣ የኃይል እና የፋይናንስ ችግሮችን በመፍታት የማምረት አቅማቸውን ወደ ከፍተኛ ደረጃ ማሸጋገር ተችሏል። በጨርቃጨርቅ፣ በቆዳ፣ በሲሚንቶ፣ በኬሚካል፣ በምግብ እና መጠጥ ዘርፎች የሚመረቱ የሀገር ውስጥ ምርቶች ከውጭ የሚገቡትን በመተካት ከፍተኛ ሀገራዊ ወጪን አስቀርተዋል።
ሲሚንቶ፣ ብረት፣ ብርጭቆ እና ሴራሚክስን የመሳሰሉ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት ብቻ ወደ 5 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ የውጭ ምንዛሬ መቆጠብ መቻሉን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ዘርፉ እያስመዘገበ ባለው ፈጣን እድገትም በማዕድን ዘርፍ 24 በመቶ፣ በማኑፋክቸሪንግ 20 ነጥብ 3 በመቶ እና በኢነርጂ ዘርፍ ደግሞ 23 በመቶ ጭማሪ መታየቱን ማንሳታቸው ዘርፉ በተደረገለት ድጋፍ ወደ ውጤታማነት መሸጋገሩን ያሳያል።
በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እና በባለሃብቶች መካከል የተደረጉ ተከታታይ ውይይቶች በዘርፉ የሚስተዋሉ ማነቆዎችን የሚፈቱ ትልልቅ ውሳኔዎች እንዲወሰኑ አስችለዋል። የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የሀገር ውስጥ ምርቶች ዕድገት እንዲጨምር አስችለዋል፤ የአምራቾችና የሸማቾችን ትስስር አጠናክረዋል እንዲሁም የህብረተሰቡን የሀገር ውስጥ ምርት የመጠቀም ባህል አሳድገዋል። በአጠቃላይ ንቅናቄው አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ ከነበረበት ፈተና ተላቆ ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል።
👉የሀገር በቀል የማክሮ ኢኮኖሚ እና የፋይናንስ ዘርፍ ሪፎርም
በኢትዮጵያ የተደረጉ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያዎችና የውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ስርዓት ለወጥ የኢንዱስትሪው ዘርፍ የነበረበትን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለማቃለል፣ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብና የሀገር ውስጥ አምራቾች ጥሬ ዕቃዎችን በነፃነት እንዲያስገቡ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል።
👉የግብርና እና ኢንዱስትሪ ትስስር
በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ትስስር ለዘላቂ እድገት፣ ለሥራ ዕድል ፈጠራ እና ለውጭ ምንዛሬ ግኝት ዕድገት መሠረታዊ ምሰሶ ናቸው። ግብርናው ለኢንዱስትሪው ጥሬ ዕቃ የሚያቀርብ ሲሆን፣ ኢንዱስትሪው ደግሞ የግብርና ምርቶችን እሴት በመጨመርና መልሶ ለግብርናው ዘርፍ ግብዓቶችን በማቅረብ ባለሁለት ወገን ትስስር ይፈጥራሉ።
👉በተወሰዱ እርምጃዎች የተመዘገቡ ውጤቶች
የመደመር መንግስት እና ባለድርሻ አካላት የኢንደስትሪ ዘርፉን ውጤታማነት ለማሳደግ ባደረጉት የተቀናጀ ጥረት እና በተወሰዱ መዋቅራዊ ማሻሻያዎች የፋብሪካዎች የማምረት አቅምን 67 በመቶ ማድረስ ተችሏል። ይህ ቀደም ሲል 30 እና 40 በመቶ ከነበረው የፋብሪካዎች የማምረት አቅም አንጻር ሲታይ ከፍተኛ ለውጥ መምጣቱን የሚያመላክት ነው።
ኢትዮጵያ በመደመር እሳቤ በመመራት ባለፉት ዓመታት የኢንደስትሪ ዘርፏን ለማሳደግ በርካታ ተግባራትን በማከናወን እና የማሻሻያ እርምጃዎችን በመውሰድ በዘርፉ እምርታዊ ውጤት አስመዝግባለች። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የ2018 “ኢትዮጵያ ታምርት” ኤክስፖን አስመልክቶ ባስተላለፉት መልእክት በውጤት ተኮር አመራር ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ መልኩ የኢንዱስትሪ መስፋፋት መንጸባረቁን መናገራቸው ይህንኑ የሚገልጽ ነው፡፡
እመርታውን በተጨባጭ ማሳያ ሲያቀርቡም የአምራች ኢንዱስትሪዎችን አማካይ የማምረት አቅም ከ47 በመቶ ወደ 67 በመቶ ከፍ ማድረግ መቻሉን፣ ከ2 ሺህ 800 በላይ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንቶችን መሳብ መቻሉን እንዲሁም አዳዲስ ኢንዱስትሪ ፓርኮች መገንባታቸውንና በሀገር ውስጥ ምርትን በማስፋፋት እስከ 5 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ የውጭ ምንዛሬ መቆጠቡን መግለጻቸውም እንዲሁ።
የመደመር መንግስት በአምራች ኢንዱስትሪዎች ላይ ይስተዋል የነበረውን የፋይናንስ ማነቆ ለመፍታት በወሰደው እርምጃ፣ ቀደም ሲል 40 ቢሊዮን ብር የነበረውን የብድር መጠን ወደ 115 ቢሊዮን ብር ከፍ ማድረግ መቻሉንና የኢንዱስትሪዎችን ተወዳዳሪነት፣ ምርታማነት፣ ትርፋማነት እና የመስፋፋት ዕድል ከፍ እያለ መምጣቱን የኢንደስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል መግለጻቸው የመንግስት ውሳኔዎች ውጤታማነትን የሚያረጋግጡ ናቸው።
የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ የንግድ ሚዛንን በማጣጣም በኩል ያለውን አስተዋጽኦ ሲገልጹም የኢትዮጵያን ዘላቂ ተወዳዳሪነት ለማረጋገጥ ከፍተኛ ድርሻ አበርክቷል። በዚህ መነሻነትም መንግስት በ2019 በጀት ዓመት ከወጭ ንግድ የሚገኘውን ገቢ ወደ 1 ቢሊዮን ዶላር ለማድረስ ዕቅድ ነድፎ ለስኬታማነቱ እየታተረ ይገኛል። እነዚህ የፖሊሲም ሆነ ሌሎች የመንግስት እርምጃዎች በሙሉ የዘርፉን ውጤታማነት ለማሳደግ ያለውን ቁርጠኝነት ያረጋግጣሉ።
👉ማጠቃለያ
የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ጉዞ ከብዙ መሰናክሎች በኋላ በተለይ የመደመር መንግስት ለዘርፉ በሰጠው ከፍተኛ ትኩረት እና በወሰዳቸው የፖሊሲና የመዋቅራዊ ማሻሻያ እርምጃዎች፣ የሀገር ውስጥ ምርታማነትን በማስቀደም በሂደት ወደ ጠንካራ መዋቅር እየተሸጋገረ ይገኛል። አሁን የተጣጣሙት የፖሊሲ እርምጃዎች እና የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች ተጠናክረው ሲቀጥሉ፣ ዘርፉ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በጽኑ መሰረት ላይ በመገንባት በአፍሪካ የማኑፋክቸሪንግ ማዕከል የሚያደርግ ትልቅ አቅም አለው።